JW subtitle extractor

የቤቴል አገልግሎት—‘የምታደርጉት ነገር ሁሉ’ ወሳኝ ክፍል

Video Other languages Share text Share link Show times

ኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ቁጥር 17 ላይ እንደተገለጸው
ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦
“በመዳብ ፋንታ ወርቅ፣
በብረት ፋንታ ብር [አመጣለሁ]።”
በዚህ ትንቢት አማካኝነት ይሖዋ የድርጅቱ ምድራዊ ክፍል
ደረጃ በደረጃ ጥራቱ እንደሚጨምር ቃል ገብቷል።
ባለፉት ዓመታት ውስጥ
የተለያዩ ማስተካከያዎችን እንድናደርግ ረድቶናል።
ይህ ደግሞ በቤቴል የሚከናወነውን ሥራ ይጨምራል።
በቤቴል ውስጥ የሚከናወነው ሥራ
ሁለት ወሳኝ ዓላማዎች አሉት።
መንፈሳዊ ምግብ በተቻለ መጠን
ለብዙዎች እንዲደርስ ማድረግና
ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ መደገፍ።
የበላይ አካሉ በቤቴል ማንኛውንም ማስተካከያ የሚያደርገው
እነዚህን ሁለት ዓላማዎች ለማሳካት ነው።
ባለፉት ዓመታት ውስጥ በሕትመት ዘዴዎች፣
በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና
በግንባታ ዘዴዎች ላይ ማስተካከያ ተደርጓል።
የተለያዩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ተቀላቅለዋል።
ሌሎች ለውጦችንም መጥቀስ ይቻላል።
በዓለም ዙሪያ የሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ
በቆላስይስ 3 ቁጥር 23 ላይ የሚገኘውን ምክር በመከተል
እነዚህን ማስተካከያዎች ደግፏል።
ጥቅሱ፦ “የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን
ለይሖዋ እንደምታደርጉት በማሰብ በሙሉ ነፍሳችሁ አድርጉት” ይላል።
ብዙዎች ለበርካታ ዓመታት በታማኝነት በቤቴል በማገልገል
እነዚህ ማስተካከያዎች ሲደረጉ በዓይናቸው አይተዋል።
ልክ እንደ ይሖዋ እኛም ለዚህ ቅዱስ አገልግሎት
ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያቀርቡትን እናደንቃለን።
እነዚህ ወንድሞችና እህቶች
“እነሆኝ! እኔን ላከኝ!” በማለት የተናገረውን
የኢሳይያስን መንፈስ ያንጸባርቃሉ።
በዓለም ዙሪያ ለቤቴል የሚያመለክቱ
ወጣት ወንድሞች ቁጥር እየጨመረ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በመስኩ ላይ የሚያገለግሉ
የሠለጠኑ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች ያስፈልጋሉ።
የበላይ አካሉ በቤቴልና በመስኩ ላይ ያለውን ሁኔታ በማጤን
ከዚህ በፊት የቤቴል አገልግሎት በሚታይበት መንገድ ላይ
ለውጥ እንዲደረግ ወስኗል።
ከአሁን በኋላ የቤቴል አገልግሎት
የዕድሜ ልክ ምድብ እንደሆነ ተደርጎ አይታይም።
ቤቴል ወንድሞችና እህቶች ይሖዋን በትጋት የሚያገለግሉበትና
ለድርጅቱ የሚጠቅም ሥልጠና የሚያገኙበት ቦታ ሆኖ ይቀጥላል።
ሆኖም አሁን የምንፈልገው
እነዚህ ወንድሞችና እህቶች የሚያገኙትን ሥልጠና
መስኩ ላይ ወይም ሌላ አስፈላጊ ቦታ ላይ እንዲጠቀሙበት ነው።
ለዚህም ሲባል በቤቴል
የተለያዩ ማስተካከያዎች እንደሚደረጉ ስንገልጽላችሁ ደስ ይለናል።
አንደኛ ከመስክ ወደ ቤቴልና ከቤቴል ወደ መስክ
በየጊዜው የምድብ ለውጥ ይኖራል።
ቅድም እንደተገለጸው የቤቴል አገልግሎት
ከአሁን በኋላ ቋሚ ምድብ ተደርጎ አይታይም።
አዳዲሶቹን ቤቴላውያን የሚያሠለጥኑ ተሞክሮ ያላቸው፣
በዕድሜ የጎለመሱ ወንድሞችና እህቶች ሁሌም የሚያስፈልጉ ቢሆንም
ወደ ቤቴል የሚጠሩት ብዙዎቹ ለተወሰነ ጊዜ ያገለግላሉ፣
ሥልጠና ያገኛሉ፣ ተሞክሮ ያካብታሉ፣ ሌሎችን ያሠለጥናሉ፣
ከዚያ ሥልጠናውን መስኩ ላይ ይጠቀሙበታል።
እያንዳንዱ ቤቴላዊ በአገልግሎት ጊዜው ውስጥ
ሥልጠናውን የት ቢጠቀምበት እንደሚሻል የሚገመገምበት
አስቀድሞ የተወሰነ ጊዜ ይኖራል።
የተደረጉት ለውጦች ምን ጥቅም እያስገኙ ነው?
ከዚህ ቀጥሎ የሚቀርቡትን ቃለ መጠይቆች
እንድትከታተሉ እንጋብዛችኋለን።
በቤቴል ያገኘሁት ሥልጠና በጣም ጠቅሞኛል።
አስተዋይ እንድሆን ረድቶኛል።
ቤቴል ውስጥ በይሖዋ ከሚታመኑ
ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር ሠርቻለሁ።
አሁን ያለሁበት ጉባኤ ውስጥ
ሽማግሌ ሆኜ የተሾምኩት በቅርቡ ነው።
በዚህ ኃላፊነት ሳገለግል
በይሖዋ መታመን እንዳለብኝ ከእነሱ ተምሬያለሁ።
ወንድሞችን ለመርዳት የቻልኩትን ሁሉ
ማድረግ እንዳለብኝ የተማርኩትም ከቤቴል ነው።
የምድብ ለውጡን እንደሰማን
የወንጌል መጻሕፍትን ሀ ብለን በድጋሚ ለማንበብ ወሰንን።
በቃ፣ በወቅቱ በጣም የሚያስፈልገኝ ይሄ ነበር።
ሐሳቡን ድሮም አንብበነዋል።
ግን እዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ስናነበው
ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደን አረጋገጥን።
ውሳኔው ድርጅቱን እንደሚጠቅምም አስተዋልን።
ይሖዋ በአዲሱ ምድባችንም እንዲባርከን ከፈለግን
ውሳኔውን መደገፍ አለብን።
በቤቴል ስታገለግል ከብዙ ሰዎች ጋር ትገናኛለህ።
የሥራ ባልደረቦችህ አሉ።
ቤቴልን ለመጎብኘት የሚመጡ አሉ።
ስለዚህ ድርጅቱ ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ታያለህ።
እይታህ በጉባኤ ብቻ አይወሰንም።
ሰፊ የሆነ ቤተሰብ፣
ሰፊ የወንድማማች ማኅበር እንዳለን ትረዳለህ።
ወደ ተመደብኩበት ጉባኤ የምሄደው
ይህን ተሞክሮና እውቀት ይዤ ነው።
እዚያ ያሉ ወንድሞችን ለማበረታታት እጠቀምበታለሁ።
በቤቴል ለማገልገል ግብ እንዲያወጡ አበረታታቸዋለሁ።
ከኋላችን ሆኖ እየደገፈን ያለ ትልቅ ድርጅት አለ።
ይሄ ደግሞ የይሖዋ ፍቅርና እንክብካቤ መገለጫ ነው።
በገዛ ሕይወታችን ያየናቸውን መልካም ነገሮች
ለሌሎች እናካፍላቸዋለን።
እነዚህ ተሞክሮዎች በግልጽ እንደሚያሳዩት
ቤቴል ዕድሜ ልካችንን የምናገለግልበት ቦታ ባይሆንም
ሥልጠናው የትም የማይገኝ ነው።
ይህ ሲባል ታዲያ
አሁን ቤቴል እያገለገሉ ያሉ ሁሉ
በጊዜ ሂደት ወደ መስክ ይላካሉ ማለት ነው?
አይደለም!
ቤቴል ውስጥ የጎለመሱም ሆኑ ወጣቶች ምንጊዜም ያስፈልጋሉ።
ምሳሌ 20፡29 እንደሚለው ነው፦
“የወጣቶች ክብር ጉልበታቸው ነው፤
የአረጋውያንም ግርማ ሽበታቸው ነው።”
የመጋቢት 15, 1993 መጠበቂያ ግንብ
ይህን ጥቅስ ሲያብራራ እንዲህ ይላል፦
“የጎልማሳነት ጉልበት በበርካታ ዓመታት ከተገኘ ተሞክሮና ጥበብ ጋር ሲቀናጅ
በጣም ጠንካራ ውህደት ይፈጠራል።”
የእነዚህ ቃላት እውነተኝነት በቤቴል በግልጽ ይታያል።
የአረጋውያን ጠንካራ መንፈሳዊነትና
በዓመታት የዳበረ ተሞክሮ ይፈለጋል።
ግን እንዲህ ትሉ ይሆናል፦
“ቤቴል ውስጥ ሁልጊዜ እንዲህ ዓይነት ለውጥ የሚኖር ከሆነ
በዚያ የሚከናወነው ሥራ ሳይስተጓጎል የሚቀጥለው እንዴት ነው?”
ይህ ወደ ሁለተኛው ማስተካከያ ይመራናል።
የተቀላጠፈ ሥልጠና በመስጠት ላይ ይበልጥ ትኩረት ይደረጋል።
ወንድሞችና እህቶች በተለያዩ ምድቦች ላይ ማገልገል እንዲችሉ
አስፈላጊውን ብቃት ቶሎ እንዲያዳብሩ እንፈልጋለን።
ሥልጠናው ወጣት ወንድሞች በበለጠ ፍጥነት
ኃላፊነት እንዲሸከሙ ማድረግን ይጨምራል።
በዕድሜ ከፍ ያሉት፣ ወጣቶቹን ትኩረት ሰጥተው በማሠልጠን
በቤቴል ውስጥ ተጨማሪ ሥራና ኃላፊነት መሸከም እንዲችሉ
ድጋፍ ያደርጉላቸዋል።
ይህም በቤቴል አገልግሎታቸው ይበልጥ ጠቃሚ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል።
እርዳታ በሚያስፈልግበት ሌላ መስክ እንዲያገለግሉ ያዘጋጃቸዋል።
በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚጠቅሟቸውን
ባሕርያትና ችሎታዎች እንዲያዳብሩም ያግዛቸዋል።
ቅርንጫፍ ቢሮዎች ይህን ተግባራዊ በማድረግ
ምን ጥቅም አግኝተዋል?
እስቲ አንዳንድ ወንድሞች የሰጡትን አስተያየት
ከዚህ ቀጥሎ ተከታተሉ።
ሥልጠናው በጥራትም በቅልጥፍናም እየተሻሻለ ሄዷል።
አሁን ለሁሉም አንድ ዓይነት ሥልጠና አይሰጥም።
ከዚህ ይልቅ የእያንዳንዱን ሰው ባሕርይ፣
ችሎታ፣ ጥንካሬ ግምት ውስጥ እናስገባለን።
‘ይህ ሰው ምን ድጋፍ ያስፈልገዋል?’ ብለን እናስባለን።
ስኬታማ መሆን ከፈለግን
የምንሰጠውን ሥልጠና
እንደ ሰውየው ሁኔታ ማስተካከል አለብን።
ወጣት ሳለሁ ምንም ሥልጠና አላገኘሁም ማለት ይቻላል።
ሥራ ይሰጠኛል። የሚያሠለጥነኝ ግን አልነበረም።
አሁን ድርጅቱ እያደገ ነው።
ስለዚህ ሥልጠና ወሳኝ ነው።
ደስ የሚለው አሁን ሥልጠና በደንብ እየተሰጠ ነው።
ወጣት ወንድሞችን በሚገባ ማሠልጠንና
ኃላፊነት እንዲቀበሉ ማድረግ ድርጅቱን በጣም ይጠቅማል።
ምክንያቱም ወጣቶቹ ወንድሞች ኃይል አላቸው።
አዲስ ሐሳብ ያመጣሉ።
ትላልቆቹ ደግሞ ጥበብና ተሞክሮ አላቸው።
የሁለቱ መቀናጀት ድርጅቱ ወደፊት እንዲገሰግስ ያደርጋል።
ለውጦችን ለማስተናገድም ፈጣን ይሆናል።
ሦስተኛው ጉልህ ማስተካከያ ደግሞ
ቲኦክራሲያዊ አገልግሎታቸውን ለማስፋት የሚያመለክቱ
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፈቃደኛ ሠራተኞችን
ከምንጠቀምበት መንገድ ጋር የተያያዘ ነው።
ተመላላሽ የቤቴል አገልጋዮች እንዲሁም
የርቀትና ጊዜያዊ ፈቃደኛ ሠራተኞች እንዳሉ ይታወቃል።
እነሱን ይበልጥ በጥበብ ለመጠቀም ጥረት እናደጋለን።
ይህም በቤቴል የሚያገለግለውን የሰው ኃይል
በአግባቡ በመመጠን በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች
እጅግ አስፈላጊ በሆነው
የስብከቱ ሥራ ላይ እንዲያተኩሩ ያስችላል።
ይህ ለውጥ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያስገኛል።
እስቲ ቀጣዮቹን ተሞክሮዎች እንመልከት።
አሁን የተረዳነው ነገር ቢኖር
የቤቴል አገልግሎት በቦታ የሚገደብ አይደለም።
የትኛውም የዓለም ክፍል ላይ ሆነህ
ይህን ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ ትችላለህ።
ቤቴል የገባሁት በ19 ዓመቴ ነው።
የተወሰነ ዓመት ቆይቼ ወጣሁ።
ከዚያ ትዳር መሠረትኩ።
ልጆች ወለድኩ።
ይኸው አሁን ከዓመታት በኋላ ድጋሚ ቤቴል ተጠራሁ።
እርግጥ ከቤቴ ሆኜ ነው የምሠራው።
በሳምንት ውስጥ የተወሰኑ ቀናት።
ግን በዚህ መልኩም ቢሆን ቤቴል ማገልገሌ በጣም ጠቅሞኛል።
ትልቅ ሥልጠና እያገኘሁ ነው።
ይሖዋ ድርጅቱን እንዴት እንደሚመራው
በቅርበት ለማየት ያስችልሃል።
ማስተካከያ ማድረግ ይጠይቃል።
ወንድሞች የሚኖሩት የትም ይሁን የት
ወይም ፕሮግራማቸው ምንም ይሁን ምን
ለእነሱ የሚመች ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት እናደርጋለን።
በዚህ መልኩ የርቀት ፈቃደኛ ሠራተኞች
አብረውን እንዲሠሩ እናመቻቻለን።
የእኔና የእነሱ ሰዓት አይገናኝም።
ግን ስብሰባ ሲኖር እኔም እንድገኝ ያመቻቻሉ።
ቦታ እንዳለኝና የቡድኑ አባል እንድሆንኩ እንዲሰማኝ ይደርጋሉ።
በአብዛኛው፣ ቤቴል ውስጥ
ከእገሌ ጋር ልሥራ ብለን መምረጥ አንችልም።
ደስ የሚለው ግን ይሖዋ
ለሥራው የሚሆኑ ብቃት ያላቸው ወንድሞችንና እህቶችን
ቦታው ላይ ያስቀምጣል።
አእምሯችንን ክፍት አድርገን
አዳዲስ አሠራሮችን ለመቀበል ፈቃደኞች ከሆንን
የሥራው ጥራት ሳይነካ
የቤቴላውያንን ቁጥር መቀነስ እንችላለን።
በዚህ ሂደት የተማርነው ትልቁ ነገር ይህ ነው።
የቤቴል ሥራ ፕሮግራምህን ይነካዋል።
ግን ጉባኤው ይሄን ስለሚረዳልኝ
በቤቴል አገልግሎቴ ደስተኛ ነኝ።
በዓለም ዙሪያ ባሉ ቅርንጫፍ ቢሮዎች
እነዚህን ማስተካከያዎች ሥራ ላይ እያዋልን ነው።
ደረጃ በደረጃ ማለት ነው።
ከወዲሁ አስደሳች ውጤቶችን ማየት ጀምረናል።
የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት
ወንድሞችና እህቶች ቤቴል ውስጥ ሥልጠና ማግኘት የሚችሉባቸውን
ተጨማሪ መንገዶች ማስተዋል ችለዋል።
ይህ አዲስ አሠራር ወጣቶች
ቲኦክራሲያዊ አገልግሎታቸውን ለማስፋት
ከበፊቱ የበለጠ ቅንዓት እንዲቀሰቀስባቸው አድርጓል።
በተጨማሪም መስኩ ላይ እንዲያገለግሉ የተመደቡት ወንድሞችና እህቶች
ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ በመደገፍ ረገድ
ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሆነ
ቅርንጫፍ ኮሚቴዎች ሪፖርት አድርገዋል።
ብዙዎች አገልግሎታቸውን አስፍተዋል።
እንዲሁም በአንዳንድ መስኮች እገዛ ለማበርከት ራሳቸውን አቅርበዋል።
ለምሳሌ በአካባቢ ንድፍና ግንባታ ሥራ ይካፈላሉ።
በሆስፒታል አገናኝ ኮሜቴ ውስጥ ይሠራሉ።
በልዩ የጋሪ ምሥክርነትም ይሳተፋሉ።
አንዳንዶች የመንግሥቱ ሰባኪዎች
ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውረዋል።
ሌሎች በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተካፍለዋል።
የመሳሰሉት . . .
እነዚህ ሦስት ማስተካከያዎች ተጨማሪ ወንድሞችና እህቶች
በቤቴል በማገልገል ሥልጠናና ተሞክሮ እንዲያገኙ ያስችላሉ።
እነሱም ያገኙትን ሥልጠና
ይሖዋን በተለያዩ መንገዶች ለማገልገል ይጠቀሙበታል።
ኤፌሶን 4፡16 ላይ እንደተገለጸው
‘የክርስቶስ የአካል ክፍሎች
እርስ በርስ ተስማምተው የተገጣጠሙ ናቸው።’
ይህ የሆነው እያንዳንዱ የአካል ክፍል
በአግባቡ ሥራውን ስለሚወጣ ነው።
የበላይ አካሉ፣ እነዚህ ማስተካከያዎች ሁላችንም
በአንድነት ተስማምተን መሥራታችንን እንድንቀጥልና
የክርስቶስን አመራር በፍቅር እንድንደግፍ
እንደሚያነሳሱን ተስፋ ያደርጋል።
ውድ ወጣት ወንድሞች፣ በቤቴል ማገልገል ትችሉ እንደሆነ
በጸሎት እንድታስቡበት እናበረታታችኋለን።
በ1960 በብሩክሊን ቤቴል በተገነባ አዲስ ሕንፃ ውሰና ላይ
የበላይ አካል አባል የነበረው ወንድም ፍራንዝ
አንድ ንግግር ሰጥቶ ነበር።
በንግግሩ ላይ “ቤቴል ከሁሉ የላቀው የማሠልጠኛ ማዕከል ነው” ብሏል።
ይሄን ካለ 65 ዓመታት ቢያልፉም ዛሬም ይህ እውነታ አልተቀየረም።
የቤቴል አገልግሎት ወደር የለሽ ሥልጠና የምናገኝበት መስክ ነው።
የምታገኙት ሥልጠና ራሳችሁንም ድርጅቱንም በእጅጉ ይጠቅማል።
ለአሁን ብቻ ሳይሆን ለዘላለም።
ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ቤቴልን ግብ እንዲያደርጉ እርዷቸው።
ይህ ልዩ ሥልጠና እንዲያመልጣቸው አትፈልጉም።
የቤቴል አገልግሎት ይሖዋን በሙሉ ነፍስ ማገልገል የሚችሉበት
ግሩም አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።
በምድብ ለውጥ ምክንያት ከቤቴል ለወጣችሁ ደግሞ
ፍቅራችንንና አድናቆታችንን ልናረጋግጥላችሁ እንፈልጋለን።
ቤቴል ያገኛችሁት ተሞክሮ ውድ ዋጋ አለው።
ይህን ተሞክሯችሁን ለሌሎች አካፍሉ።
ወንድሞችና እህቶች በሚያደርጉት ሁሉ
ለይሖዋ ምርጣቸውን እንዲሰጡ አበረታቷቸው።
እናንተ ያገኛችሁትን ደስታ እንዲያጣጥሙ እርዷቸው።
ምሳሌነታችሁ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል።
የረዳችኋቸው ሰዎች ያሳያችኋቸውን ፍቅር ፈጽሞ አይረሱትም።
በእርግጥም ኢሳይያስ 60፡17 ላይ እንደተገለጸው
ይሖዋ በድርጅቱ ውስጥ የሚያስፈልገውን ነገር እያየ
የቤቴልን አሠራር እያሻሻለው እንደሚሄድ እንተማመናለን።
ሁላችሁም ለይሖዋም ሆነ
ለድርጅቱ ባላችሁ ፍቅርና ታማኝነት ተነሳስታችሁ
የምታደርጉትን ማንኛውንም ነገር
በሙሉ ነፍስ እንደምታደርጉት ሙሉ እምነት አለን።
አሁንም ሆነ ለዘላለም!