JW subtitle extractor

JW ብሮድካስቲንግ—መጋቢት 2026

Video Other languages Share text Share link Show times

ወንድሞችና እህቶች እንኳን ደህና መጣችሁ!
አንዳንድ ጊዜ የሚያጋጥሙን ችግሮች
እንዴት እንደምንወጣቸው ግራ የሚያጋቡ ናቸው።
እንዲህ ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን
ስሜታችንን መቆጣጠር የምንችለው እንዴት ነው?
የዮናስን መጽሐፍ በጥልቀት በመመርመር
ታማኝ ፍቅርን በተመለከተ ግሩም ትምህርት እናገኛለን።
ዝናና ሀብት ከፍተኛ የማታለል ኃይል አላቸው።
ከታዋቂነት ይልቅ ይሖዋን ማገልገል የመረጠችን
የአንዲት እህታችንን ተሞክሮ እንሰማለን።
በሙዚቃ ቪዲዮአችን ላይ ደግሞ ወንድሞቻችን እስር ቤት ቢጣሉም
ጠንካራ እምነት ይዘው መቀጠል የቻሉት እንዴት እንደሆነ እናያለን።
ይህ JW ብሮድካስቲንግ ነው።
“ልባችሁ አይረበሽ።”
ኢየሱስ ለሐዋርያቱ እንዲህ ያላቸው
ከእነሱ ጋር እንደማይቆይ ከነገራቸው በኋላ ነው።
ፊታቸው ላይ የሐዘንና የድንጋጤ ስሜት ይነበባል።
በዚህም ምክንያት እነሱን ለማበረታታት
ዮሐንስ 14፡1 ላይ እንዲህ አለ፦
“ልባችሁ አይረበሽ።
“በአምላክ እመኑ።
በእኔም ደግሞ እመኑ።”
መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ ክፉዎችን
ከሚናወጥ ባሕር ጋር ያመሳስላቸዋል።
እኛም አንዳንድ ጊዜ እንደ እነሱ ይሰማናል።
አንድን መጥፎ ዜና ገና ሰምተን ሳንጨረስ
ሌላኛው ደግሞ ይከተላል።
በዓለም ላይ የሚከሰቱት ነገሮችም ሆነ የግል ችግሮቻችን
እንድንዝልና እንድናዝን ያደርጉናል።
ብዙውን ጊዜ አንድን ቀን ስናገባድድ
‘ኃይሌ ተሟጥጧል፤
ከአሁን በኋላ ምንም ማድረግ አልችልም’ እንላለን።
ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የተናገራቸው ቃላት
ከሚያዝሉ ነገሮች እንድንርቅና
ኃይላችንን በትክክለኛው ቦታ ላይ እንድንጠቀምበት ይረዱናል።
እስቲ ኢየሱስ የተናገራቸው ሁለት ዓረፍተ ነገሮች
በዚህ ረገድ የሚረዱን እንዴት እንደሆነ እንይ።
“ልባችሁ አይረበሽ” ከሚለው እንጀምር።
‘ልባችሁ እንዲረበሽ አትፍቀዱ’ ተብሎም ሊተረጎም ይችላል።
‘ልባችሁ እንዲረበሽ አትፍቀዱ’ ሲል
ሐዋርያቱ ሊቆጣጠሩት የሚችሉት ነገር እንዳለ እየጠቆማቸው ነው።
ሐዋርያቱ ልባቸው እንዲረበሽ መፍቀድም ሆነ
ልባቸው እንዳይረበሽ መቆጣጠር ይችሉ ነበር።
ብዙውን ጊዜ አንድ ስሜት የሚፈጠረው ከምናስበው ነገር ነው።
ለምሳሌ ስለ አንድ ሰው፣ ስለ አንድ ነገር
ወይም ስለ አንድ ድርጊት ስናስብ
በስሜታችን ላይ የሚያመጣው ለውጥ አለ።
ስለዚህ ልባችሁ እንዲረበሽ አትፍቀዱ ሲል
‘አስተሳሰባችሁን መቆጣጠር ትችላላችሁ’ እያለን ነው።
በሌላ አባባል ስለ አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ካሰብን ማዘናችን አይቀርም።
አንድ ውሳኔ ስናደርግ ውጤቱን ካላወቅን ልንጨነቅ እንችላለን።
አእምሯችንን ከአንድ ትልቅ ቤት ጋር ልናመሳስለው እንችላለን።
ብዙ ክፍሎች ካሉት።
እያንዳንዱ ክፍል በሕይወታችን ውስጥ የሚገጥመንን አንድ ሁኔታ ይወክላል እንበል።
ስለዚህ አንደኛው ክፍል ውስጥ ስንቆይ
ስሜታችን ክፍሉ ከሚወክለው ድርጊት ወይም ክስተት ጋር ይያያዛል።
በዚህ ወቅት ሐዋርያቱ
‘ኢየሱስ ትቶል ሊሄድ ነው’ የሚል ክፍል ውስጥ ነበሩ።
ስለዚህ ከፍተኛ ሐዘን ተሰምቷቸው ነበር።
ግን ኢየሱስ ስሜታቸውን መቆጣጠር እንደሚችሉ አረጋግጦላቸዋል።
ደቀ መዛሙርቱ ሙሉ በሙሉ በሐዘን ስሜት ተውጠው መቆየት
ወይም ስሜታቸውን ተቆጣጥረው
በይሖዋና በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳላቸው ማሳየት ይችሉ ነበር።
ይሄ ለእኛ ጥሩ ማሳሰቢያ ነው።
የምናስበውን ነገር በመምረጥ ስሜታችንን መቆጣጠር እንችላለን።
አንዳንድ ጊዜ ልክ እንደ ሐዋርያቱ
ሐዘንና ጭንቀት ወዳለበት ጨለማ ክፍል ውስጥ ልንገባ እንችላለን።
ግን ይህን አስታውሱ፦
በዚህ ክፍል ውስጥ እንደ እንግዳ ናችሁ።
ስለዚህ ክፍሉ ውስጥ ላለመቆየት ጥረት አድርጉ።
ልባችን እንዳይረበሽ ማድረግ የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ
ኃይላችንንና ስሜታችንን ከሚያሟጥጡ ነገሮች መራቅ ነው።
ኢሳይያስ 55፡2 እንዲህ ይላል፦
“ምግብ ላልሆነ ነገር ለምን ገንዘባችሁን ታወጣላችሁ?
እርካታ ለማያስገኝ ነገርስ ለምን ገቢያችሁን ታባክናላችሁ?”
ምግብ ላልሆነ ነገር ገንዘብ ማውጣት እንደማንፈልግ ሁሉ
ፈጽሞ እርካታ በማያስገኙ ነገሮች ኃይላችንን ማባከን አንፈልግም።
ለምሳሌ ያህል የአንድ ቀን ምግብ ለመግዛት
አሥር ዶላር ተሰጣችሁ ብለን እናስብ።
ሆኖም ለቁርስ ብቻ ስምንት ዶላር ብታወጡ
ለምሳና ለራት የሚሆን በቂ ገንዘብ አይኖራችሁም።
እኛም ብንሆን በየቀኑ የሚኖረን ኃይል በጣም ውስን ነው።
ስለዚህ ‘ምን ላይ እናውለው’ የሚለውን በጥንቃቄ ማሰብ አለብን።
ታዲያ ኃይላችሁን የምትጠቀሙት እንዴት ነው?
ስለዚህ ‘ኃይሌን የማውለው
በእርግጥ በሚያስፈልጉ ነገሮች ላይ ነው?’
ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ።
ለምሳሌ እየነዳችሁ ሳለ ሌላ መኪና ጥልቅ አለባችሁ እንበል።
ወይም ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጸመባችሁ፣
አሊያም አንድ ሰው አስከፋችሁ እንበል።
እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ከልክ በላይ በመናደድ
ኃይላችን ሊሟጠጥ ይችላል።
ግን እስቲ አስቡት።
ኃይላችሁን በዚህ መንገድ ማባከናችሁ ምክንያታዊ ነው?
‘ኃይሌን የማውለው እርካታ በማያስገኙና
እርባና ቢስ በሆኑ ነገሮች ላይ ነው’ ብላችሁ ጠይቁ።
ደግሞም ለማታውቁት ሰው የገንዘብ ቦርሳችሁን ሰጥታችሁ
የፈለከውን ያህል ውሰድ ትሉታላችሁ?
ለምታምኑትና ለምትወዱት ሰው ትሉ ይሆናል።
ለማታውቁት ሰው ግን እንዲህ እንደማትሉ ግልጽ ነው።
በተመሳሳይም ኃይላችንን ይበልጥ አስፈላጊ
በሆኑ ነገሮች ላይ መዋል ይኖርብናል።
ይህም ለቤተሰቦቻችን፣ ለወንድሞቻችን፣ ለእህቶቻችን
በተለይ ደግሞ ለአምልኳችንና
ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ለመግለጽ ልንጠቀምበት ይገባል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢንተርኔት፣ ፊልም፣ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ ጉዳዮች
ኃይላችንን ሊያሟጥጡ የሚችሉ ነገሮች ናቸው።
የገንዘብ ቦርሳችንን ላገኘነው ሰው እንደማንሰጥ ሁሉ
ኃይላችንንም በእነዚህ ነገሮች ላይ ማባከን አንፈልግም።
በእነዚህ ነገሮች ኃይላችን ከተሟጠጠ
ለምንወዳቸው ሰዎች የምናውለው ኃይል አይኖረንም።
ያለንን ውስን ኃይል ለምንወዳቸው ሰዎችና
አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች የምናውል ከሆነ
በሕይወታችን ደስተኞች ልንሆን እንችላለን።
ብዙ ሰዎች እነሱን የሚያስደስታቸውን ነገር ሁሉ
በገንዘብ በመግዛት ደስታ እንደሚያገኙ ይሰማቸዋል።
ሆኖም ራስ ወዳድነት ፈጽሞ ደስታ ሊያስገኝ አይችልም።
ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሏል።
ከዚህ አባባል በስሜት እንዳንዝልና
ኃይላችንን በምን ነገር ላይ መዋል እንዳለብን ጥሩ ትምህርት እናገኛለን።
ደስታን በዚህ መንገድ ልንገልጸው እንችላለን፦
ደስታ ለሌሎች ፍቅር ስናሳይ የምናገኘው ውጤት ነው።
ለምሳሌ እሳት ስናቀጣጠል ምን ውጤት እናገኛለን?
ሙቀትና ብርሃን!
ሙቀትና ብርሃንን ማግኘት የምንፈልግ ከሆነ
እሳት ማቀጣጠል ይኖርብናል።
እሳቱን ለማያያዝ ወይም ለማቀጣጠል ግን ጥረት ይጠይቃል።
ጥረት ማድረጋችን ብርሃንና ሙቀት እንድናገኝ ያስችለናል።
ኃይላችንን ለሌሎች ፍቅር እንዳለን የሚያሳዩ ነገሮችን ለማድረግ ስንጠቀምበት
በምላሹ ደስተኞች እንሆናለን፤ እርካታም እናገኛለን።
ኢየሱስ “ልባችሁ አይረበሽ” ማለቱ
አስተሳሰባችን አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ
ስሜታችንን መቆጣጠር እንደምንችል ያስገነዝበናል።
እንዲሁም ኃይላችንን በጥበብ በመጠቀም
ለቤተሰባችን፣ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን
በተለይ ደግሞ
ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ለማሳየት ልንጠቀምበት እንችላለን።
እስቲ አሁን ደግሞ የዮሐንስ 14፡1ን ሁለተኛውን ክፍል እንመልከት።
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎአቸዋል፦
“በአምላክ እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ።”
ኢየሱስ እዚህ ላይ እንዲሁ እመኑ ብቻ አላለም።
እምነት በባሕርይው ከአንድ ነገር ጋር ተያይዞ መገለጽ ይኖርበታል።
ለዚህ ነው ኢየሱስም እምነትን ከእሱና ከይሖዋ ጋር አያይዞ የገለጸው።
ስለዚህ ስትረበሹ ወይም ስትጨነቁ
ይሖና ኢየሱስ ከጎናችሁ እንደሆኑ አስቡ።
ችግሮቻችሁን ለዘለቂታው ለማስወገድ እየሠሩ ነው።
ቅርብ ባለ ሌላ ክፍል ውስጥ እንዳሉ አድርጋችሁ አስቡ።
በፈለጋችሁት ጊዜ ወደዚያ ክፍል መሄድ ትችላላችሁ።
በጸሎትና በማሰላሰል!
ይሖዋ ዛሬ ያሉትን ችግሮች በሙሉ ለማስተካከል
አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ እንዳለው ማወቃችን ስሜታችንን ያረጋጋልናል።
ኢየሱስ ‘ሁሉንም ነገር በራሴ ላስተካክል’
የሚል ዝንባሌ እንደሚያጠቃን ያውቃል።
በተራራ ስብከቱ ላይ እንዲህ ብሏል፦
“መጨነቃችሁን ተዉ።”
ለምን?
“ምክንያቱም በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ
እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል።”
ታዲያ ይሖዋ እንደሚያያችሁና
የሚያስፈልጋችሁን እንደሚያውቅ ታምናላችሁ?
እንዳትረበሹ የሚረዳችሁ እንዲህ ያለው እምነት ነው።
ለይሖዋ መተው ያለብንን ችግር በራሳችን ለመፍታት መሞከራችን
ጭንቀታችን እንዲጨምር ያደርጋል።
ለምሳሌ ጦርነትን፣
ሕዝባዊ ዓመፅን
ድህነትን፣
እርጅናን፣
ወንጀልን
ማስወገድ ትችላላችሁ?
እንዲህ ያሉ ትላልቅ ነገሮችን ስናስብ
እኛ ልንፈታቸው እንደማንችል አምነን እንቀበላለን።
እነዚህን ችግሮች የሚፈቱት ይሖዋና ኢየሱስ ብቻ ናቸው።
የአምላክ መንግሥት ሲመጣ!
በተለይ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ስንጋፈጥ
ወይም መጥፎ ዜናዎችን ስንሰማ
ስሜታችንን የሚያረጋጋልን በይሖዋና በኢየሱስ መታመን ነው።
ለምሳሌ እኔ፣ እንደ ኤርትራ
ወይም እንደ ሩሲያ ባሉ አገሮች ውስጥ ስለሚኖሩ ወንድሞች ሳስብ
የተጨነቅኩባቸው ጊዜያት ነበሩ።
እናንተም እንዲህ ተሰምቷችሁ ያውቅ ይሆናል።
ስሜት የሚደቁስ ነገር ነው።
ታዲያ ኢየሱስ እንዳለው ልባችን እንዳይረበሽ
ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
እኔን የረዳኝ እንዲህ ብዬ መጠየቄ ነው፦
‘ጉባኤው ማድረግ ያለበትን ሁሉ አድርጓል?’
‘ቅርንጫፍ ቢሮው፣ ዋናው መሥሪያ ቤት ማድረግ የሚችሉትን አድርገዋል?’
‘እኔስ ስለ እነሱ ጸልያለሁ?’
የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ አዎ ከሆነ
‘ይሖዋ ማድረግ የምንችለውን አድርገናል።
አሁን ጉዳዩ ባንተ እጅ ነው’ እላለሁ።
መዝሙር 112፡7
አንድ ጻድቅ ሰው ክፉ ወሬ ሲሰማ ምን እንደሚያደርግ ይገልጻል።
ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦
“ክፉ ወሬ አያስፈራውም።
በይሖዋ ስለሚተማመን ልቡ ጽኑ ነው።”
ክፉ ወሬን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት እንደሚረዳን በመታመን!
አንዳንዴ ካጋጠማችሁ ችግር የተነሣ እንደዛላችሁ ሲሰማችሁ
ይሖዋ ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል
ሊሰጣችሁ ቃል እንደገባ አስታውሱ።
ይሖዋ ይህን ቃሉን እንደሚጠብቅ እምነት ይኑራችሁ።
ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ይሰማናል።
እንዲሁም ያጋጠመንን ችግር ለመወጣት የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል።
ይሖዋ ያጋጠመንን ችግር ባያስወግድልን እንኳ
ችግሩን በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል።
ሮም ምዕራፍ 12 ቁጥር 11
“በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ” ይለናል።
ይህ ጥቅስ አንድ ነገር ያስታውሰኛል።
ይህ ድንጋይ እንዲሁ ተራ ድንጋይ አይደለም።
ላዩ ላይ ለየት ያለ ብርሃን ሲያርፍበት ድንጋዩ ያንጸባርቃል።
ብርሃን ካላረፈበት ግን እንደ ማንኛውም ተራ ድንጋይ ነው።
ይህ ለየት ያለ ብርሃን ሲያርፍበት ግን
እንዴት እንደሚያንጸባርቅ አያችሁ?
እኛም የይሖዋ መንፈስ ሲያርፍብን እንደዚህ ነው የምናንጸባርቀው።
ይሖዋም በተመሳሳይ ቅዱስ መንፈሱን በመጠቀም
በየዕለቱ እንድንታደስ ያደርገናል።
በምሳሌያዊ ሁኔታ እንድናንጸባርቅ ይረዳናል።
ለምሳሌ አንድ ትንሽ ልጅ ምሽት ላይ በጣም ፈራ እንበል።
ሮጦ የሚሄደው የት ነው?
ወላጆቹ ጋ!
እንደሚረዱት እርግጠኛ ነው።
እኛም ስንጸልይ ይሖዋ ወዳለበት ክፍል እየሮጥን ነው።
የሚሰማንን እንንገረው።
እሱ ደግሞ ያጽናናናል።
በመንፈሱ፣ በመጽሐፍ ቅዱስና በወንድሞቻችን ተጠቅሞ።
በምሳሌያዊ ሁኔታ መብራቱን እኛ ላይ በማብራት
ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል ይሰጠናል።
ልባችን እንዲሸበር የሚያደርግ ነገር ሲያጋጥመን
ቤቱ ውስጥ ሌሎች ክፍሎችም እንዳሉ እናስታውስ።
ወደ ይሖዋ ስትጸልዩና መጽሐፍ ቅዱስን ስታነቡ
ይሖዋ በቤቱ ውስጥ ወዳለ ሌላ ክፍል ወስዷችሁ
ከእናንተ ጋር ጊዜ እያሳለፈ እንደሆነ አድርጋችሁ አስቡ።
ሐዘን አጋጥሟችኋል?
ወደ ትንሣኤ ክፍል ያስገባችኋል።
አሟችኋል?
ፍጹም ጤና ወዳለበት ክፍል ያስገባችኋል።
በሠራችሁት ስህተት ተሸማቃችኋል?
ወደ ይቅርታ ክፍል ይወስዳችኋል።
ሐዋርያቱ ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ሲያዩት
ምን ተሰምቷቸው ሊሆን እንደሚችል አስቡት።
መጀመሪያ ላይ ‘ውይ ኢየሱስ ጥሎ ልሄድ ነው’
የሚል ክፍል ውስጥ ነበሩ።
አሁን ግን ‘ኢየሱስ ተመልሶ ከእኛ ጋር ሆኗል’
የሚል ክፍል ውስጥ ገቡ።
በእርግጥም በይሖዋና በኢየሱስ ማመናቸው ክሷቸዋል።
ንግግራችንን ለማጠቃለል፣
ኢየሱስ በዮሐንስ 14፡1 ላይ ከተናገረው ሐሳብ
ያገኘናቸውን ትምህርቶች ለመከለስ እንሞክር።
ኢየሱስ “ልባችሁ አይረበሽ” ወይም ‘ልባችሁ እንዲረበሽ አትፍቀዱ’ ማለቱ
ያጋጠመን አስቸጋሪ ሁኔታ በስሜታችን ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ
መምረጥ እንደምንችል ይጠቁማል።
በስሜት እንድንዝል ከሚያደርጉ ነገሮች በመራቅ
ኃይላችንን ለቤተሰባችን፣ ለወንድሞቻችን
ከሁሉ በላይ ደግሞ ለአምላካችን ለይሖዋ አገልግሎት እናውለው።
ኢየሱስ በመቀጠል
“በአምላክ እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ” ብሎናል።
በይሖዋና በኢየሱስ ካመንን እኛ የማንችለውን ነገር ለእነሱ እንተወዋለን።
ዛሬ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ችግር
ይሖዋ ወደ ፊት ሙሉ በሙሉ ያስተካክለዋል።
እስከዚያው ግን
በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚያጋጥሙንን የተለያዩ ችግሮች ለመቋቋም
ይሖዋ ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል እንደሚሰጠን እምነት ይኑረን።
ስለዚህ ከአሁን በኋላ ልባችሁ ሲረበሽ ወይም ስትዝሉ
ኢየሱስ በዮሐንስ ምዕራፍ 14፡1 ላይ የተናገረውን
የሚከተለውን ሐሳብ አስታውሱ።
“ልባችሁ አይረበሽ።
በአምላክ እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ።”
ዮናስ የይሖዋ አገልጋይ ነበር።
ግን በአምላክ መታመንን መማር አስፈልጎታል።
ይህን ወሳኝ ትምህርት ካገኘ በኋላ
ስሜቱን በተሻለ መንገድ መቆጣጠር የሚችል ሰው ሆኗል።
ውድ ሀብት ለማግኘት ቆፍሩ በተባለው በቀጣዩ ቪዲዮ ላይ
ከዮናስ የምናገኛቸውን ሌሎች ትምህርቶችም እናያለን።
አባ፣ የዮናስን ቪዲዮ ስላየን ደስ ብሎኛል።
በጣም አሪፍ ቪዲዮ ነው።
ልክ ነህ፣ ከቪዲዮው ብዙ እንማራለን።
መጽሐፍ ቅዱስን በመመርመር ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ ትምህርቶች እናገኛለን።
‘ዘገባው ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል?’
ብለን መጠየቃችን ጥሩ ነው።
ቆይ ልጻፈው።
ታዲያ ምን ትምህርት አገኘህ?
ይሖዋ ትግዕሥተኛና ይቅር ባይ መሆኑን።
ልክ ነህ፣ ዮናስ በመንፈሳዊ እድገት እስኪያደርግ ይሖዋ ታግሶታል።
ዮናስ 3:1 ላይ እንደምናየው ሁለተኛ ዕድል ሰጥቶታል።
የተሳሳተ ውሳኔ በማድረጉ ችግር ላይ ሲወድቅም ይሖዋ አልተወውም።
አመለካከቱንም እንዲያስተካከል በደግነት አርሞታል።
ሲገርም! ተስፋ አልቆረጠበትም።
አዎ፣ በሌላ አባባል ታማኝ ፍቅር አሳይቶታል።
ግን፣ ታማኝ ፍቅር ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ታስታውሳለህ?
መሰለኝ።
ስናጠና ማድረግ ያለብን ሌላው ነገር
የማናውቃቸውን ቃላት ፍቺ መፈለግ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስህን ከፍተህ ታማኝ ፍቅር ብለህ ጻፍና ፈልግ።
ከዚያም ርዕሶች የሚለውን ንካ።
አገኘኸው?
አዎ።
ጎበዝ!
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፍቻው ላይ ምን ይላል?
እስቲ አንብበው።
“ታማኝ ፍቅር በከፍተኛ ቅንዓት፣ በጽኑ አቋም፣ በታማኝነትና
ከልብ በመነጨ የመውደድ ስሜት ተነሳስቶ ፍቅር ማሳየትን ያመለክታል።”
ይሖዋ ለዮናስ ያደረገው እንደዚ ነው።
አገልጋዮቹን ስለሚወዳቸው ሁልጊዜም ይረዳቸዋል።
ዮናስ ግን ይሄ ቶሎ አልገባውም።
ከማዕበል ተርፎ፣ ሦስት ቀን ዓሣ ሆድ ውስጥ አሳልፎ፣
የነነዌ ሰዎች ሲገቡም አይቶ የሚያስበው ስለራሱ ብቻ ነበር።
ይሖዋ ነነዌን ባለማጥፋቱ ዮናስ በጣም ተበሳጭቷል።
ሐሰተኛ ነብይ እንዳይባል ፈርቶ ይሆናል።
ይህን ሁሉ አሳልፎም ሰዎች እሱ እንደተሳሳተ ከሚያስቡ
ነነዌ እንድትጠፋ መርጧል።
አዎ፣ ዮናስ ትክክል አልነበረም።
ግን ይሖዋ ምን የሚያደርግ ይመስልሃል?
እንኳን ይሖዋ እንደ እኔ አልሆነ!
እርግጥ ዮናስ እንደዚህ ዓይነት ምላሽ ቢሰጥም መጥፎ ሰው አልነበረም።
ይሖዋም አንድን የቅል ተክል ተጠቅሞ እርማት ሰጠው።
ምዕራፍ 4 ቁጥር 6ን እስቲ እየው። ምን ይላል?
ፀሐዩ እንዳያቃጥለውና አረፍ እንዲል ቅል እንዳበቀለለት ይናገራል።
የሚገባው ባይሆንም ይሖዋ ለእሱ ደግ ነበር።
ጥቅሱ ዮናስ በቅሏ እጅግ እንደተደሰተ ይናገራል።
ስለዚህ ይሖዋ ታማኝ ፍቅር ስላሳየው የዮናስ ስሜት ተቀይሯል።
አሁን ይሖዋ ዮናስን የሚያስተምርበት ጥሩ አጋጣሚ ተፈጠረ።
ምን የሚያስተምረው ይመስልሃል?
ሌላ ትምህርት ደግሞ ሊማር ነው።
ልክ ነህ፣ ይሖዋ የቅል ተክሉን እንዲበላ አንድ ትንሽዬ ትል ላከ።
ተክሏም ደረቀች።
በዚህ ጊዜ ዮናስ ምን ተሰማው?
ድጋሚ ተቆጣ።
ልክ ነህ፣ ይሖዋም ቆም ብሎ እንዲያስብ አደረገው።
አዎ፣ ቁጥር 10 እና 11 ላይ የሚገርም ትምህርት ነው የሰጠው።
አዎ ‘አንተ ለዚህች ተክል ካዘንክ
እኔ ለነነዌ ሰዎችና እንስሳት ላዝን አይገባም’ ብሎ ጠየቀው።
ታሪኩ የሚያበቃው እዚህ ላይ ነው።
ዮናስ ይሖዋ የተናገራቸውን እነዚህን ቃላት በማስፈር ዘገባውን ደምድሟል።
ነጥቡ ገብቶታል።
ሰዎችን ይሖዋ በሚያይበት መንገድ ማየት እንዳለበት ተምሯል።
ይሖዋ ዮናስን መርዳት መቀጠሉ ገርሞኛል።
ምንም ቢፈጠር ታማኝ ፍቅሩን ማሳየቱን ቀጥሏል።
ልክ ነህ፣ ምርምራችንን እንቀጥል።
ከይሖዋ ታማኝ ፍቅር ጥቅም ያገኘው ዮናስ ብቻ ነበር?
በእምነታቸው ምሰሏቸው የሚለው መጽሐፍ ላይ
እንዲህ የሚል ምክር ተሰጥቶናል።
“በዓይነ ሕሊናችሁ ለመመልከት ጣሩ።
“የተሰማቸው ስሜት ይሰማችሁ።
“እነሱ ያዩትን ነገር እናንተም ለማየት ጣሩ።
እናንተ ብትሆኑ ምን ታደርጉ እንደነበር ለማሰብ ሞክሩ።”
እስቲ ዮናስ ምን ተሰምቶት እንደነበር ለማሰብ ሞክር።
በእሱ ስህተት ምክንያት መርከበኞቹ ምንም ምላሽ ወደማይሰጧቸው
የሐሰት አማልክት ሲጮሁ ሲመለከት ምን ተሰምቶት ይሆን?
የእሱ ጥፋት እንደሆነ ነግሯቸውም ወደ ባሕሩ ሊጥሉት አልፈለጉም።
ልክ ነው፣ እሱን ለማዳን የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል።
ይሖዋ እሱን የማያመልኩት እነዚያ መርከበኞች የነበሯቸውን ጥሩ ባሕርያትና
ምን ያህል ተጨንቀው እንደነበር ዮናስ እንዲያስተውል ፈልጓል።
ልክ ነህ፣ ዮናስ መርከበኞቹን ይሖዋ በሚያይበት መንገድ ማየት ጀምሮ ይሆን?
ይገርማል!
ግን ይሖዋ ዮናስን መጀመሪያውኑ
እሱን ወደማያመልኩ የባዕድ አገር ሰዎች የላከው ለምንድን ነው?
ለምን ይመስልሃል?
ምናልባት የነነዌ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ፈልጎ ይሆን?
ልክ ነህ፣ ታዲያ ይሖዋ ያሳየው ፍቅር እነማንን ጠቅሟል?
እ . . .
ይሖዋ ለዮናስ ታማኝ ፍቅር አሳይቶታል።
ለመርከበኞቹና ለነነዌ ሰዎችም ፍቅር አሳይቷቸዋል።
ልክ ነህ፣
በትንሣኤ ሲነሳ ዮናስ ከባድ ስህተት በሠራበት ወቅት የተከናወነውን ነገር
ይሖዋ ስለ ልጁ ለማስተማር እንደተጠቀመበት ማወቁ አይቀርም።
ኢየሱስም በስም እንደጠቀሰውና ወደፊት የሚያጋጥመውን ነገር ለመግለጽ
የእሱን ታሪክ እንደጠቀሰ ሲያውቅ ምን እንደሚሰማው አስብ።
በጣም ደስ ይላል።
ይሖዋ ፍጹም የሆነ የፍቅር ምሳሌ ነው።
ታዲያ እኛ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
አንዱ መንገድ ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ይመስለኛል።
አንዳንዴ ከቤት ወደ ቤት ሳገለግል
ሰዎች ጥሩ ምላሽ ስለማይሰጡ ከባድ ይሆንብኛል።
ከዛ ግን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የእኔ ስሜት እንዳልሆነ አስታውሳለሁ።
ትልቁ ነገር ይሖዋ በሰዎች ተስፋ ስለማይቆርጥ
እኔም ተስፋ መቁረጥ የለብኝም።
ጎበዝ የእኔ ልጅ፣ እውነትህን ነው።
ነጥቡ ገብቶሃል።
እኔን ደግሞ ይህ ዘገባ ‘አልችለውም’ ብዬ የማስበው ሥራ ሲሰጠኝ
የተጨነኩባቸውን ጊዜያት አስታውሶኛል።
መጀመሪያ ላይ ጥሩ ምላሽ ያልሰጠሁባቸው ጊዜያት አሉ።
የሚጸጽቱኝን ነገሮችም ተናግሬ አውቃለሁ።
ከዚያ ግን የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል።
ይሖዋ እነዚያን ጊዜያት ሁሌ እያስታወሰ እንደማይቆይ ማወቄ አጽናንቶኛል።
የልባችንን ያውቃል።
ለውጥ እንድናደርግም በትዕግሥት ይጠብቀናል።
ስለ ይሖዋ ምን ያህል ተምረናል ብለን በመጠየቅ፣
የማናውቃቸውን ቃላት ፍቺ በመፈለግና
በዓይነ ሕሊናችን በመሳል ብዙ ትምህርት አግኝተናል።
ልክ ነህ፣ ግን ገና ብዙ የምንማረው አለ።
ለምሳሌ ራሳችንን በዮናስ ቦታ እናስቀምጥና
በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ይሖዋ እንዲረዳው ሲጸልይ
የነበረውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናችን በመሳል ምን እንማራለን?
ለነነዌ ሰዎች መስበክ ዮናስ ያሰበውን ያህል
ከባድ እንዳልነበረ ማስተዋላችን ምን ያስተምረናል?
እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው ያገኘነው!
ዮናስ ስሜታዊ መሆኑ መጥፎ ሰው ነው አላስባለውም።
ይሖዋ ለዮናስና ለነነዌ ሰዎች ስላሳየው ፍቅር ስታነቡ
ተጨማሪ ዕንቁዎች ማግኘታችሁ አይቀርም።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጉባኤዎች በጉጉት የሚጠብቁት አንድ ልዩ ሳምንት አለ።
ከወረዳ የበላይ ተመልካቹና ከሚስቱ ጋር የሚያሳልፉት ሳምንት!
ይህ አበረታች ዝግጅት የጀመረው እንዴት እንደሆነ
በቀጣዩ ቪዲዮ ላይ እንመልከት።
ጉባኤያችንን የወረዳ የበላይ ተመልካች
የሚጎበኝበት ሳምንት ልዩ ጊዜ ነው።
በዚያ ሳምንት በአገልግሎት እንጠመዳለን፤
አበረታች ንግግሮች እንሰማለን፤
አብረን ጥሩ ጊዜም እናሳልፋለን።
ግን የወረዳ ሥራ የጀመረው እንዴት ነው?
ምን ለውጦችስ ተደርገዋል?
ታሪካችን ከየት ወዴት?
የተባለው ይህ ክፍል መልሱን ይሰጠናል።
ሥራው የጀመረው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ነው።
እንደ ጳውሎስ፣ በርናባስና ጢሞቴዎስ ያሉ ወንድሞች
ወደተለያዩ ቦታዎች በመጓዝ ጉባኤዎችን ያበረታቱ ነበር።
በዛሬው ጊዜ ያለው የይሖዋ ድርጅትም ይህንኑ ምሳሌ በመከተል
ከ1894 ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ቡድኖች
እንዲጎበኙና እንዲያበረታቱ ተወካዮችን መላክ ጀመረ።
ከጊዜ በኋላ እነዚህ ወንድሞች
ፒልግሪምስ ተብለው መጠራት ጀመሩ።
ፒልግሪሞች ወደተለያዩ ጉባኤዎች እየተጓዙ
ከወንድሞች ጋር አንድ ወይም ሁለት ቀን ያሳልፋሉ።
ወንድሞችንም ያበረታታሉ።
እርግጥ ጉዞ በጣም ከባድ ነበር።
ለምሳሌ የኤድዋርድ ብሬንሰንን ጉዞ እንመልከት።
በምዕራባዊ ዩናይትድ ስቴትስ የምትገኝን
አንዲት ትንሽ መንደር ለመጎብኘት መጀመሪያ በባቡር ይጓዛል።
ከዚያም ሌሊቱን ሙሉ በሰረገላ ሲጓዝ ያድራል።
ቀጥሎም አመቺ ባልሆነ ሌላ ዓይነት ሰረገላ ይሳፈርና
ወደ ተራራማው አካባቢ አስቸጋሪ ጉዞ ያደርጋል።
ፒልግሪሞች ጎበዝ አስተማሪ ብቻ ሳይሆን
ትሑት መሆንም ነበረባቸው።
አሌክሳንደር ግርሃም ለዚህ ምሳሌ ነው።
ወንድም ግርሃም አስደሳች ንግግሮችን የሚሰጥ ቢሆንም
ንግግሮቹ ትንሽ ይረዝማሉ።
አንዳንዴ እንዲያውም ለሰዓታት!
ወንድም ራስል ይህን ሲሰማ
ለወንድም ግርሃም እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፈለት፡-
ውድ ወንድም፣ ያለህን ፍቅርና ቅንዓት በሚገባ አውቃለሁ።
ግን እውነትን ለሰዎች የማካፈል ጉጉትህ
ሰዓቱ ሲሄድ እንዳይታወቅህ ሊያደርግ ይችላል።
ወንድም ግርሃም ምክሩን በትሕትና ተቀብሏል።
ከዚያ በኋላ የሚሰጣቸው ንግግሮች
ማራኪ ግን አጠር ያሉ ሆነዋል።
መጀመሪያ ላይ የፒልግሪሞች ዋነኛ ኃላፊነት ንግግር መስጠት ነበር።
በ1920ዎቹ ግን ይህ ሁኔታ ተቀየረ።
ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት
ግንባር ቀደም ሆነው መሳተፍ ጀመሩ።
በመሆኑም መጠሪያቸው ተቀይሮ
የአካባቢ የአገልግሎት ዳይሬክተሮች
ከዚያም የአካባቢ አገልጋዮች ተባሉ።
ስያሜው ወንድሞችን በአገልግሎት ለመደገፍ
የሚያደርጉትን ጥረት የሚያጎላ ነው።
ከዚያ በኋላ ደግሞ ሌላ ትልቅ ለውጥ መጣ።
በ1930ዎቹ አሜሪካ ውስጥ
በስብከቱ ሥራ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ተነሳ።
ይህን ተጽዕኖ ለመቋቋም
ጉባኤዎች አንድ ላይ ለመስበክ ለየት ያለ ዝግጅት አደረጉ።
ይህም አንድነታቸውን አጠናክሮላቸዋል።
በኋላም ድርጅታዊ አሠራሩን ይበልጥ ለማቀላጠፍ
20 የሚያክሉ ጉባኤዎችን ያቀፉ ዞኖች ተቋቋሙ።
አንድ የዞን አገልጋይ እያንዳንዱን ጉባኤ እንዲጎበኝ ይመደባል።
በየተወሰነ ጊዜው በዞኑ ውስጥ ያሉት ጉባኤዎች
አንድ ላይ ሆነው የዞን ስብሰባ ያደርጋሉ።
አሁን ወረዳ ስብሰባ የምንለውን ማለት ነው።
በ1940ዎቹ ደግሞ ሌላ ስያሜ ተሰጣቸው።
የወንድሞች አገልጋዮች ተባሉ።
ከነዚህ ወንድሞች አንዱ አንጄሎ ካታንዛሮ ነው።
ወንድም ካታንዛሮ ይህ ኃላፊነት የተሰጠው በ19 ዓመቱ ነው።
‘ሁልጊዜ በጉዞ ላይ ያለሁ አገልጋይ ነኝ’ ይል ነበር።
አሜሪካ ውስጥ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ባገለገለባቸው
ከ60 የሚበልጡ ዓመታት ውስጥ
እሱና ባለቤቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች፣
እንዲሁም አዳዲስ ሰዎች መንፈሳዊ ዕድገት እንዲያደርጉ ረድተዋል።
ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች መጀመሪያ የወረዳ አገልጋዮች፣
ቀጥሎም የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የሚል ስያሜ ተሰጣቸው።
እነዚህ ወንድሞችና ሚስቶቻቸው
በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ
ብዙ መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች ሆነዋል።
የራሴ የሚሉት ቤት ሳይኖራቸው
ከቦታ ወደ ቦታ እየተጓዙ አገልግለዋል።
ያውም ረጅም ርቀት እየተጓዙ!
ብዙዎቹ የዊንስተን ፔንንና የባለቤቱን ስሜት ይጋራሉ።
ፔንና ባለቤቱ የወረዳ ሥራ የጀመሩት
በደቡብ ፓስፊክ ሲሆን ዕድሜያቸው 20ዎቹ ውስጥ ነበር።
ደሴቶቹ ላይ ከፍተኛ ሙቀትና የወባ ትንኞች አሉ።
አንዳንዴም የምግብ እጥረት ያጋጥማል።
ያም ቢሆን ወንድሞች ባሳዩአቸው ፍቅርና አሳቢነት የተነሳ
የአገልግሎት ምድባቸውን ወደውታል።
በዛሬው ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞች
በወረዳ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል።
በ1999 ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያስችል ሥልጠና መሰጠት ጀመረ።
ለወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀው ትምህርት ቤት
አሁን በዓለም ዙሪያ እየተሰጠ ነው።
የተጓዥ የበላይ ተመልካቾች መጠሪያ ብዙ ጊዜ ተለዋውጧል።
ያልተለወጠ ግን አንድ ነገር አለ።
እንደ ጳውሎስ ዘመን ሁሉ
በዛሬው ጊዜ ያሉ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸውም
ያላቸውን ሁሉ፣ ራሳቸውንም ጭምር ለመስጠት ፈቃደኞች ናቸው።
ወጣቶችን ጨምሮ ጉባኤውን በሙሉ ያበረታታሉ።
ስለዚህ በቀጣዩ የወረዳ የበላይ ተመልካች ጉብኝት ወቅት
ለሚከፍሉት መሥዋዕትነት ያላችሁን አድናቆት ለማሳየት ለምን አትሞክሩም?
ታሪካችን ከየት ወዴት?
በሚለው ዓምድ ቀጣይ ክፍል ላይ
የይሖዋን ሕዝቦች ታሪክ ሌላ ገጽታ እንዳስሳለን።
እስከዚያው ደህና ሁኑ!
የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ
የወረዳ የበላይ ተመልካቾችንና ሚስቶቻቸውን ስለሰጠን ይሖዋን እናመሰግነዋለን።
ከወረዳ የበላይ ተመልካቹ፣ ካገባ ደግሞ ከሚስቱ ጋር ያሳለፋችሁት
ትዝ የሚላችሁ አስደሳች ጊዜ አለ?
የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በይሖዋ አገልግሎት
ይበልጥ እንድትሳተፉ አበረታቷችሁ ሊሆን ይችላል።
የወረዳ የበላይ ተመልካች መሆን የሚችለው ሁሉም ሰው አይደለም።
ግን ሁላችንም ለሰዎች የሚያሳዩትን ፍቅር መኮረጅ እንችላለን።
አንዳንዶች ራሳቸውን ከሁኔታዎች ጋር በማስማማት
አገልግሎታቸውን ያሰፉት እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ
ብዙ ልናከናወን የምንችለው ነገር እንዳለ ስናውቅ ወደዚያ ተዛወርን።
በኬቺያ ቦሊቪያኖ ጉባኤ ማገልገል ከጀመርን አራት ዓመት ሆኖናል።
ፈርናንዶ እባላለሁ።
እኔ ሚካኤላ።
አርጀንቲና ውስጥ ኢንሂሬኖ ኤርጎ በተባለው ቦታ
በኬቺያ ቦሊቪያኖ ጉባኤ እያገለገልን ነው።
በጎረቤት አገር በቦሊቪያ ሥራ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው።
ስለዚህ ብዙዎች ወደ አርጀንቲና መጥተው
በእርሻ ቦታዎች ላይ ይሠራሉ።
ሥራው ጉልበት የሚጠይቅና አድካሚ ነው።
አንዳንድ ጊዜ እስከ ምሽቱ አምስት
ወይም ስድስት ሰዓት ድረስ አምሽተው ይሠራሉ።
ሥራው የሚጠይቀውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው።
እነሱን ለማነጋገር ምቹ የሆነው ጊዜ
ከሰዓት ወደ ሥራ ከመመለሳቸው በፊት ነው።
በዚህ ሰዓት አብዛኛውን ጊዜ ሙቀቱ
40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ስለሚደርስ
መስበክ በጣም ከባድ ነው።
የሥራቸው ሁኔታ ስለሚያስገድድ
ጥናቶቻችንን ብዙ ጊዜ የምናስጠናው
እዛው ሥራ ላይ እያሉ ነው።
ስለዚህ እነሱ እርሻው ላይ የተለያዩ ሥራዎችን በሚሠሩበት ጊዜ
እኛ እየተከተልን ጥቅሶች ወይም አንቀጾቹን እናነብላቸዋለን።
ለምሳሌ የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስናሳያቸው
ሰምተውት የማያውቁት ከሆነ
ወይም ሌላም ነገር ሆኖ ትኩረታቸውን ከሳበው
ሥራቸውን ቆም ያደርጋሉ።
ይህም የበለጠ ማወቅ እንደሚፈልጉ ይጠቁማል።
በእዛ ሰዓት የሚሠሩት ግድ ስለሆነባቸው ብቻ ነው።
ብዙ ጊዜ እስኪጨርሱ ድረስ እንድንጠብቃቸው ይጠይቁናል።
በዚህ ጊዜ ሥራቸውን ቶሎ እንዲጨርሱ እናግዛቸዋለን።
መጀመሪያ አካባቢ ብዙዎቹ ይገረማሉ።
‘የእውነት ልታግዙት ነው?
ግን እኮ ልብሳችሁ ይቆሽሻል’ ይሉናል።
እኛ ግን እነሱም በማገዛችን ደስተኞች ነን።
ደግሞም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል።
በጊዜ ሂደት ወዳጆች ሆንን።
ደግሞም የሚፈለገው ይሄ ነው።
እድገት እንዲያደርጉ መርዳት የምንችለው ወዳጅ ከሆንን ብቻ ነው።
ወዳጅ መሆናችን ከልብ እንደምናስብላቸው ያረጋግጥላቸዋል።
ማገልገል እወዳለሁ።
ለእኔ ፈጽሞ መሥዋዕትነት መክፈል እንደሆነ አይሰማኝም።
ስሜ ቶኒ ማሬሮ ነው።
እኔ ደግሞ ማሪሉዝ።
የመጣነው ከስፔን ነው።
አሁን የምናገለግለው ደግሞ በፓራጓይ ነው።
በኮቪድ ወቅት ከቤት ላይ ላለመውጣት የቻልነውን ያህል ተጠንቅቀናል።
ብዙ ማስተካከያ ማድረግ ነበረብን።
በጊዜው በጣም የከበደኝ የማላውቀውን ሰው ሳላየው በስልክ ማነጋገር ነው።
ይህ በጣም ነበር የሚያስጨንቀኝ።
አንድ ቀን አንድ ሰው ጋ ለመጀመሪያ ጊዜ ደወልኩና
ጥናት መጀመር ይችል እንደሆነ ጠየኩት።
በጣም የሚገርመው ሰውየው ጥናት ለመጀመር ተስማማ።
ከዚያም ‘አስበህበት ልትመልስልኝ የምችለው ጥያቄ
ነገ በቴክስ ብልክልህስ?’ አልኩት።
እሱም ተስማማ።
መጀመሪያ ላይ ቶሎ መልስ ስላልሰጠኝ
ፍላጎት የሌለው መስሎኝ ነበር።
ግን ምሽት ላይ መልስ ጻፈልኝ።
ከጊዜ በኋላ ግን በጣም ሥራ የሚበዛበት ሰው እንደሆነ ተረዳሁ።
ከጠዋት እስከ ማታ ሁልጊዜ ሥራ ላይ ነው ማለት ይቻላል።
ይህን ሳውቅ እኔም ማስተካከያ አደረግኩ።
ከዚያም አንድ ቀን
‘ባለቤትህስ ጥናቱ ላይ መገኘት ትችላለች?’ ብዬ ጠየቅሁት።
እሱም ‘አዎ’ አለኝ።
ግን ለወራት ልናገኛት አልቻልንም።
እሱን ለማስጠናት፣
ማጥናት እችላለሁ ብሎ እስኪደውልልን ድረስ ቁጭ ብለን መጠበቅ ነበረብን።
አዎ ሁሌ ዝግጁ ነበርን።
ከምሽቱ ሦስት ሰዓት፣ አራት ሰዓት፣
ወይም አምስት ሰዓትም ቢሆን መደወሉ አይቀርም።
‘በአምስት ደቂቃ ውስጥ ዝግጁ እሆናለሁ’ ብሎ መልእክት ይልካል።
ከዚያም ሊታጠብ ሲሯሯጥ እናየዋለን።
ዝግጁ ሲሆን ቁጭ ይልና ማጥናት እንጀምራለን።
መጀመሪያ ላይ ከባድ ሥራ ሆኖብኝ ነበር።
አዎ ልክ ነው።
ከዚያ ግን እየለመድነው ስንሄድ በጣም ወደድነው።
ምክንያቱም ካጠናን በኋላ ሁል ጊዜ የሚሰማን ደስ የሚል ስሜት ነው።
ከጥናቱ በኋላ እየተያየን ‘ይህ ነገር ግን የእውነት ነው’ እንባባል ነበር።
አዎ ልክ ነው።
ግን ይህን ያህል ፍላጎት አላቸው ማለት ነው?
አዎ እውነትም ደግሞ ፍላጎት ነበራቸው።
ጥናቱን ይፈልጉት ነበር።
ደግሞም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተማሩትን ተግባራዊ አድርገው
ከአንድ ዓመት በኋላ ተጠመቁ።
ሳስበው ደስ ይለኛል።
ያደረግነው ጥረት መልሶ ስለካሰን
ይሖዋን በየለቱ አመሰግነዋለሁ።
ከልቤ አመሰግነዋለሁ።
ቅን የሆኑ ሰዎችን እነሱ በሚፈልጉት ጊዜና ቦታ ማስተማር
መሥዋዕት መክፈል ይጠይቃል።
ያም ቢሆን አንድ ሰው ወደ ይሖዋ እንዲቀርብ ለመርዳት
የምንከፍለው መሥዋዕትነት ፈጽሞ አያስቆጭም።
ከ20 ዓመታት በፊት የእህት ሮሳሊያ ፊልፕስ ተሞክሮ
ንቁ! መጽሔት ላይ ወጥቶ ነበር።
ከበርካታ ዓመታት በፊት ያደረገችው ውሳኔ
እሷንም ሆነ በዙሪያዋ ያሉትን ሰዎች የጠቀመው እንዴት ነው?
የተወለድኩት ታዋቂ ዘፋኞችና ተዋንያን ካሉበት ቤተሰብ ነው።
በጣም ዝነኛው አባቴ ይመስለኛል።
ኸርማን ቫልዴስ ይባላል።
በአብዛኛው የሚታወቀው ግን ቲንታን ተብሎ ነው።
ሙዚቃ ሕይወቴ ነበር።
ከልጅነቴ ጀምሮ ስሜቴን የምገልጸው በሙዚቃ ነበር።
የሆነ ነገር ሲሰማኝ ጊታሬን አንስቼ ሙዚቃ አቀናብራለሁ።
ሙዚቃን እንደ ሥራ እይዘዋለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም።
የምፈልገው ያን አልነበረም።
ሆኖም የ 15 ዓመት ልጅ እያለሁ አባቴ ሞተ።
ስለዚህ ቤተሰባችንን በገንዘብ ለመደገፍ ሥራ መያዝ ነበረብኝ።
አንድን የሙዚቃ ቡድን ተቀላቀልኩ።
ከዚያም ታዋቂ ተዋናይና ዘፋኝ ሆንኩ።
ከጊዜ በኋላ ግን አብሬያቸው የምሠራቸው ሰዎች
ጥሩ ሥነ ምግባር እንደሌላቸው ተገነዘብኩ።
ስለሆነም በሰዎች ላይ እምነት መጣል አቃተኝ።
እውነትን ስማር ግን ቅን ከሆኑ፣
እኔን ከልብ ከሚወዱኝና ደስ ከሚሉ ሰዎች ጋር ተገናኘሁ።
ከዚያ እኔም መለወጥ ጀመርኩ።
በቃ የተለየ ሰው ሆንኩ።
ደስተኛ፣ ፍልቅልቅና ተጫዋች ሰው ሆንኩ።
ወላጅ እንደመሆናችን መጠን
ወደ ሜክሲኮ ስንመለስ በዋነኝነት ያሳሰበን ነገር
‘ልጆቻችን በመዝናኛው ዓለም ተስበው ወደዚያ ቢገቡስ’ የሚለው ነበር።
እኔና ባለቤቴ ልጆቻችን እንዲህ ያለ ነገር እንዳያጋጥማቸው
የተቻለንን ሁሉ አድርገናል።
በአንድ ወቅት ሜክሲኮ ሲቲ ውስጥ
ከአንድ ታዋቂ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቀጠሮ ነበረኝ።
ወደዚያ የሄድኩት ከ 17 ዓመቷ ልጄ ከጂያና ጋር ነበር።
እዛም ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች እየፈለገ የሚቀጥር አንድ ሰው አያት።
‘አንቺም ትዘፍኛለሽ’ ሲላት
‘አዎ’ አለችው።
ስትዘፍን ሰማትና ድምጿን በጣም ወደደው።
ስለዚህ ወዲያውኑ ወደ ቢሮ ወሰዳትና እንድትቀመጥ ጋበዛት።
እንዲህ ሲላት ሰማሁ፦
‘እየውልሽ እዚህ የቴሌቪዥን ጣቢያ ውስጥ ሥራ እንቀጥርሻለን።
‘ታዋቂ ሰው እናደርግሻለን።
‘ኮንትራት አዘጋጅልሻለሁ።
ሰኞ መጥተሽ እንፈራረማለን።’
ጂያና ከቢሮው ስትወጣ በጣም ፈርቼ ነበር።
ከዚያም “ግብዣውን ተቀበልሽ?” አልኳት።
እሷም እንዲህ አለችኝ፦
“ኧረ በፍጹም እማዬ።
“ከምንም ነገር በላይ የሚያስደስተኝ ይሖዋን ማገልገል ነው።
የአቅኚነት አገልግሎቴን በጣም ነው የምወደው” አለችኝ።
በጣም የሚያስገርመው ከአንድ ሳምንት በኋላ
ቤቴል ውስጥ በአንድ የሙዚቃ ፕሮጀክት ውስጥ
እንድትካፈል የሚጋብዝ ደብዳቤ ደረሳት።
ያንን የሚያምረውን ድምጿን ይሖዋን ለማወደስ ተጠቀመችበት።
አሁንም በፕሮጀክቶች ላይ ትካፈላለች።
ላለፉት በርካታ ዓመታት
ይሖዋ ለእኔና ለልጄ ቤቴ ውስጥ
በሙዚቃ ፕሮጀክቶች ውስጥ የመካፈል መብት ሰጥቶናል።
ሰይጣን ትኩረቴን በተለያዩ ነገሮች ለመከፋፈል ይሞክራል።
ለምሳሌ በአንድ ወቅት አባቴን በሚዘክር ሥራ ላይ
እንድካፈል ኮንትራት ቀረበልኝ።
ሥራው በጣም ጊዜዬን የሚወስድ ነበር።
በእርግጠኝነት የዘወትር አቅኚነቴንም ይነካብኛል።
ስለዚህ ሥራውን እምቢ አልኩኝ።
ባለፉት ዓመታት ሁሉ ይሖዋ እኔን መባረኩን አላቋረጠም።
አንድ ዓይነት የሥራ ግብዣ ቀርቦልኝ እንቢ ስል
ይሖዋ ከዚያ የበለጠ ነገር ይሰጠኝ ነበር።
ለምሳሌ በተለያዩ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች የሚካፈሉ ወንድሞችን
የማስተናገድ መብት አግኝቻለሁ።
ያጋጠሙኝ ተፈታኝ ነገሮች በይሖዋ መታመንን አስተምረውኛል።
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ‘ያለ እምነት አምላክን ደስ ማሰኘት አይቻልም።
ደግሞም አምላክ ከልብ ለሚፈልጉት ወሮታ ከፋይ ነው።’
ከእናቴ ጋር ማገልገል በጣም ያስደስተኛል።
አሁን ከ90 ዓመት በላይ ሆኗታል።
በተለያዩ የአገልግሎት መስኮች መካፈል ያስደስተናል።
ባለፉት ዓመታት ውስጥ በርካታ ዘመዶቼ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳስጠናቸው ጠይቀውኛል።
አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።
ከእናቴና ከልጄ ጋር ሆነን ጊታር እየተጫወትን ስንዘምር በጣም ደስ ይለኛል።
ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ሰብሰብ ብለን አስደሳች ጊዜ እናሳልፋለን።
በአዲሱ ዓለም አባቴን የማይበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።
እቅፍ አድርጌ እቀበለዋለሁ።
ልጆቼን አስተዋውቀዋለሁ።
ከእናቴም ጋር አብረው ይሆናሉ።
አባቴ የሚነሳው
ባሕር ዳርቻ አካባቢ ይመስለኛል።
ድሮ እንደምናደርገው አብረን እንድንዘምር እፈልጋለሁ።
በግሌ ያደረኩት ውሳኔ ለዘላለም ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ መኖር ነው።
እንዴት ያለ ግሩም ተሞክሮ ነው!
እህት ሮሳሊያ በይሖዋ ታምናለች።
በዚህም የተነሳ እሷም ሆነች ቤተሰቧ ብዙ በረከቶችን አጣጥመዋል።
ይሖዋ በእሱ እንድንታመን ይፈልጋል።
በተለይ ደግሞ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ስንገባ።
ቀጥሎ ወንድም ስቲቨን ሌት ስደት ሲያጋጥመን
በይሖዋ መታመን የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራልናል።
ዛሬ እንድንነጋገርበት የመረጥኩት ርዕስ
መንፈስ ቅዱስ ስደትን እንድንቋቋም
ኃይል ይሰጠናል የሚል ነው።
መጠበቂያ ግንቡም ላይ ያለው ሐሳብ
በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚደርሱትን
የተለያዩ ዓይነት ስደቶችን ያብራራል።
የዛሬው ዕለት ጥቅሳችን የሆነው ዘካርያስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 6 ግን
የይሖዋ መንፈስ እስካለን ድረስ
ምንም ዓይነት ስደት ቢያጋጥመን
በጽናት ልንቋቋመው እንደምንችል ይነግረናል።
ግን ሰይጣን በእኛ ላይ ስደት የሚያደርስበት
ዋነኛው ዓላማ ምንድን ነው?
አዎ፣ የአምላክ ሕዝቦች ተስፋ እንዲቆርጡ
እጅ እንዲሰጡ ወይም አቋማቸውን እንዲያላሉ ነው።
እስቲ ስለ አንበሳ ባሕርይ ቆም ብለን እናስብ።
ምሳሌያዊ አንበሳ የሆነው ሰይጣን አድቅቆ ሊውጠን ይፈልጋል።
አንበሳ አንድን እንስሳ አድቅቆ ሲውጥ
የተዋጠው እንስሳ ምንድን ነው የሚሆነው?
ከአንበሳው ጋር ይዋሃድና የአንበሳው አካል ይሆናል። አይደለም?
ሰይጣንም እኛን እንዲህ ነው ማድረግ የሚፈልገው።
ሰይጣን የዚህ ዓለም ክፍል ያልሆኑት ሰዎች
የእሱ ዓለም፣ የእሱ ሥርዓት ክፍል እንዲሆኑ ይፈልጋል።
በሌላ አባባል የእሱ አካል እንዲሆኑ ማለት ነው።
እኛ የአምላክ አገልጋዮች ግን ከመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ጋር
ይህ እንዳይሆን ቁርጥ አቋም ይዘናል።
ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ እስካሁን የተጠቀማቸው
እንዲሁም ወደፊት የሚጠቀምባቸው የስደት ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው?
እስቲ አምስቱን ብቻ እንመልከት።
አርማጌዶን ከመምጣቱ በፊት
ወይ በእኛ ወይ በምንወዳቸው ሰዎች ላይ
ከእነዚህ ስደቶች የትኛው እንደሚደርስ አናውቅም።
ስለዚህ የትኛውም ዓይነት ስደት ቢያጋጠመን
ታማኝነታችንን ይዘን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።
ሌሎችም ይህንኑ እንዲያደርጉ እንርዳ።
የመጀመሪያው እገዳ ነው።
በዘመናችን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ
ከመቶ በላይ በሚሆኑ አገሮች ውስጥ ታግዶ ያውቃል።
ሥራችን ታግዶ የሚያውቀው ከአልባንያ እስከ ዙምባቡዌ ነው።
በእንግሊዝኛ ፊደላት ቅደም ተከተል
ከኤ እስከ ዜድ እንደ ማለት ነው።
እንደምናስታውሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም እገዳ ነበር።
ለምሳሌ ቤተ መቅደሱን መልሶ የመገንባቱ ሥራ በ522 ታግዶ ነበር።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሚያከናውኑት የስብከት ሥራ
በተለያዩ አካባቢዎች ታግዶ ነበር።
ይህን እገዳ ሲጥሱ ደግሞ በነገሥታትና በገዥዎች ፊት ይቀርቡ ነበር።
ግን በነገሥታትና በገዥዎች ፊት ሲቀርቡ
መንፈስ ቅዱስ ይረዳቸው የነበረው እንዴት ነው?
እኛስ እንዲህ ያለ ነገር ቢያጋጥመን እንዴት ነው የሚረዳን?
የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት
ማቴዎስ ምዕራፍ 10ን እስቲ አብረን እናውጣ።
ከቁጥር 19 ጀምሮ ያለውን ሐሳብ አብረን እናንብብ።
ማቴዎስ 10 ከ19 ጀምሮ።
“ይሁን እንጂ አሳልፈው ሲሰጧችሁ
እንዴት ወይም ምን ብለን እንመልሳለን ብላችሁ አትጨነቁ።”
እንዴት ወይም ምን ብላችሁ አትጨነቁ ያለበት ምክንያት ምንድን ነው?
“የምትናገሩት ነገር በዚያኑ ሰዓት ይሰጣችኋልና።
“በምትናገሩበት ጊዜ በምትናገሩበት ጊዜ ብቻችሁን አይደላችሁም፣
ይልቁንም በእናንተ የሚናገረው የአባታችሁ መንፈስ ነው።”
ስለዚህ ብቻችንን አይደለንም።
ድርሻችንን እንወጣለን።
ግን ጥቅሱ ላይ ቃል እንደተገባልን
ምን እንደምንናገር እንድናውቅ የሚረዳን፣
ኃይል የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ ነው።
ሁለተኛው የስደት ዓይነት ደግሞ እስር ነው።
ኢየሱስ እንደ ተናገረው የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች
በተደጋጋሚ ታስረዋል።
ሉቃስ 21፡12 ላይ እንዲህ ብሏል፦
‘ሰዎች ይይዟችኋል።
እንዲሁም ለወህኒ ቤት አሳልፈው ይሰጧችኋል።’
ይህ በእርግጥም ተፈጽሟል።
ባለፉት አሥርተ ዓመታት
የይሖዋ ሕዝቦች በተደጋጋሚ ታስረዋል።
ለምሳሌ ሩሲያና አጋሮቿ ይህን ዓይነቱን ስደት
በአምላክ ሕዝቦች ላይ ብዙ ጊዜ አድርሰዋል።
ሌሎች ብዙ መንግሥታትም ተመሳሳይ ነገር አድርገዋል።
‘በእስር ላይ ላሉት ጸልዩ’ የሚለውን ሐሳብ የምወደው ለዚህ ነው።
ወንድሞች ይህን እንድናደርግ ብዙ ጊዜ ያበረታቱናል።
በኤርትራ፣ በቱርክሜንስታን፣
በሩሲያና በሌሎችም ቦታዎች ላይ ላሉት እንድንጸልይ።
ዕብራውያን 13፡3 በዚህ ረገድ የምወደውን ሐሳብ ይዟል።
“በእስር ላይ ያሉትን ከነሱ ጋር ታስራችሁ እንዳላችሁ አድርጋችሁ በማሰብ
ሁል ጊዜ አስታውሷቸው” ይላል።
ምናልባት እኛ አሁን አልታሰርን ይሆናል።
የወደፊቱን ግን አናውቅም።
ግን ብንታሰር እንኳ
ሌሎች ከእኛ ጋር ከእኛ ጋር የታሰሩ ያህል
እንደሚጸልዩልን ማወቃችን ያጽናናናል።
ሦስተኛው የስደት ዓይነት
ልጆቻችንን ከትምህርት ቤት ማባረር ነው።
ሰይጣን ልጆችን መንካት
የወላጆችን የዓይን ብሌን እንደ መንካት እንደሆነ ያውቃል።
ወላጆች ሕመሙ ተሰምቷቸው
ታማኝነታቸውን ያጎድላሉ ብሎ ያስባል።
ይህ በ1940ዎቹ በአሜሪካ ውስጥ ትልቅ ችግር ነበር።
በይሖዋ ምሥክሮች ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ በብዙ አገራት ሥራችን ታግዷል።
እንዲሁም ልጆቻችን ከትምህርት ቤት ተባረዋል።
ይህ ሁኔታ ደግሞ በኢየሱስ ላይ ያለውን እምነት በመግለጹ ምክንያት
ከምኩራብ የተባረረውን ሰው ያስታውሰናል።
ራእይ 13፡16, 17ን መመልከታችን ደግሞ
አራተኛውን የስደት ዓይነት
ለይተን ለማወቅ ያስችለናል።
ጥቅሱ የሚናገረው
አውሬው ማለትም የሰይጣን ፖለቲካዊ ሥርዓት
ሰዎችን በመጫን ወይም በማስገደድ
ምልክቱን በእጃቸው ላይ ወይም በግምባራቸው ላይ ማድረጉን ነው።
አለዚያ መግዛትም ሆነ መሸጥ አይችሉም።
ስለዚህ ይህ ምን ዓይነት ስደት ነው?
ወንድሞቻችን ላይ የኢኮኖሚ ጫና በማሳደር
ገለልተኝነታቸውን እንዲያላሉ የሚደረግ ተጽዕኖ ነው።
ይህ ዘዴ ሰይጣን ብዙ ጊዜ የሚጠቀምበት የስደት ዓይነት ነው።
ገለልተኝነታቸውን ስለ ጠበቁ ወንድሞች ከሥራ ተባረዋል።
የንግድ ሥራቸው ማዕቀብ ተጥሎበታል።
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆንን በማላዊ የሚገኙ ወንድሞቻችን
በ25 ሳንቲም የፖለቲካ ፓርቲ ካርድ ባለመግዛታቸው
የደረሰባቸው ዘግናኝ የግፍ ታሪክ ነው።
ካርዱን መግዛት በዋጋ ሲተመን ርካሽ ሊመስል ይችላል።
መንፈሳዊ ኪሳራው ግን በዋጋ አይተመንም።
ወንድሞች አሻፈረን ያሉት ለዚህ ነው።
አምስተኛውና የመጨረሻው የምንወያይበት የስደት ዓይነት
ማቴዎስ 5፡11 ላይ የተገለጸው ነው።
ማቴዎስ 5፡11 ላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦
“በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ ስደት ሲያደርሱባችሁና
“ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲያስወሩባችሁ
ደስተኞች ናችሁ።”
ስደቱ ምን ዓይነት ነው?
ስም ማጥፋት!
ብዙ ጊዜ በመገናኛ ብዙሃን ስማችን ይጠፋል። አይደል?
መሪያችን ኢየሱስ እንኳ ስሙ ጠፍቷል።
አጋንንት ያለበት፣ ተሳዳቢ፣ ሆዳም፣ ሰካራም ተብሏል።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችም ስማቸው ጠፍቷል።
የአይሁድ መሪዎች ሥራ 28፡22 ላይ እንደተዘገበው ጳውሎስን እንዲህ ብለውታል፦
“ሆኖም ስለዚህ ኑፋቄ በየቦታው መጥፎ ነገር እንደሚወራ ስለምናውቅ
ያንተን ሐሳብ ደግሞ መስማት ተገቢ ይመስለናል።”
እውነትም በዚያ ጊዜ ስማቸው ጠፍቷል።
ግን ስማችን ቢጠፋም
ይህን ስደት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መቋቋም እንችላለን።
ስለዚህ እስካሁን
አምስት የስደት ዓይነቶችን ተመልክተናል።
ሥራችን ላይ እገዳ መጣል፣
እስር፣ ልጆቻችንን ከትምህርት ቤት ማባረር፣
ገለልተኝነታችንን እንድናላላ የኢኮኖሚ ጫና ማሳደር
እንዲሁም ስም ማጥፋት።
ያላነሳናቸው የስደት ዓይነቶችም አሉ።
ግን ምንም ዓይነት ስደት ቢያጋጥመን
ከመንፈስ ቅዱስ በምናገኘው እርዳታ
ለይሖዋ አምላክ ታማኝ ሆነን መቆም እንችላለን።
አሁን ግን አንድ ጥያቄ ይነሳል።
መንፈስ ቅዱስን ማግኘትና በእሱ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
ሦስት መንገዶችን ባጭሩ እንመልከት።
አንደኛ ሉቃስ 11:13 ላይ
ኢየሱስ “በሰማይ ያለው አባታችሁ
ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸዋል” ብሏል።
ስለዚህ እንጸልይ።
ሁለተኛው ነገር ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ተስማምቶ መሥራት ነው።
በመሰብሰብ፣ በማገልገል እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብ።
ሦስተኛው ኤፌሶን 4፡30 እንደሚለው
የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አለማሳዘን ነው።
ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ላይ ሙሉ በሙሉ
እንዳይሠራ ከሚያደርግ ነገር ሁሉ እንርቃለን።
መንፈሱን እንድናገኝ እንጸልያለን። አብረነውን እንሠራለን።
እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን ከሚያሳዝን ነገር እንርቃለን።
እነዚህን እስካሁን ያየናቸውን ነገሮች ካደረግን
በአጽናፈ ዓለማችን ውስጥ ከሁሉ የላቀው ኃይል በአራት መንገዶች ያበረታናል።
በየትኞቹ መንገዶች?
ሦስቱን ኢየሱስ ዮሐንስ 14፡26 ላይ ነግሮናል።
መንፈስ ቅዱስ ረዳት ይሆነናል።
ሁለተኛው ነገር ያስተምረናል።
እንዲሁም ኢየሱስ ያስተማረንን እንድናስታውስ ያደርገናል።
ስለዚህ መንፈስ ቅዱስን ‘አስታዋሽ’ ልንለው እንችላለን።
አስታዋሽ የሚለውን ቃል አስታውሱ።
ስደት በሚደርስብን ጊዜ
ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን አስታዋሽ እንዲያደርግልን እንጸልይ።
በዚያ ሰዓት ማሰብ ያለብንን ነገር እንዲያስታውሰን ማለት ነው።
ከመንፈስ ቅዱስ ኃይል የምናገኝበት ሌላው መንገድ ደግሞ
ኢየሱስ ዮሐንስ 16:13 ላይ
“ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” ያለው ነው።
ስለዚህ አራቱ ነገሮች መንፈስ ቅዱስ ረዳት ይሆነናል፣
ያስተምረናል፣
ያስታውሰናል፣ እንዲሁም ይመራናል።
አደገኛ ፈንጂዎች የተቀበሩበትን ቦታ ማቋረጥ ቢኖርባችሁ
ቦታውን የሚያውቅና የሚረዳችሁ ሰው ብታገኙ
ደስ እንደሚላችሁ ግልጽ ነው።
የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ስናገኝ ውጤቱ ምን ይሆናል?
ምንም ዓይነት ስደት ቢያጋጥመን
ሰይጣን አድቅቆ ሊውጠንና ወደ እሱ ዓለም ሊቀላቅለን አይችልም።
የዚህ ዓለም ክፍል አንሆንም።
ስለዚህ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለው
የይሖዋን ቃል እኛም እናስተጋባለን።
በወታደራዊ ኃይል ወይም በራሳችን ጉልበት ሳይሆን
ይሖዋ በሚሰጠን ቅዱስ መንፈስ
ስደትን መቋቋም እንችላለን።
በጽንፈ ዓለም ውስጥ እጅግ ታላቅ ከሆነው ኃይል
በፈለግን ጊዜ ብርታት ማግኘት እንደምንችል ማወቄ
ሁልጊዜ እጅግ ያስደንቀኛል።
በዚህ ወር የሙዚቃ ቪዲዮ ላይ
አንድ ወጣት ወንድም አስቸጋሪ ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜ
መንፈስ ቅዱስ በተስፋው ላይ እንዲያተኩር የረዳው
እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክሩ።
ይሖዋ፣ ጻድቅ ነህ፤
ፍትሕ ነው መንገድህ።
ንጹሐኑ ሲጨቆኑ፣
መች ይችላል ልብህ?
ግፉ በዝቶ፣ መከራዬ፣
ቢፈስም እንባዬ፤
ለመታገሥ መርጫለሁ፤
በቀል ያንተ ነው።
ትቼዋለሁ በ’ጆችህ፤
ፍረደኝ ዳኛዬ።
አውቃለሁ፣ አላፍርም፤
አንተን አቤት ብዬ።
ወህኒ ብወርድ፣ ቢፌዝብኝ
ምንም አይበግረኝ፤
ባለሥልጣን፣ ወዳጅ ዘመድ
አንዳች አያስፈራኝ!
ልጋፈጠው ቆርጫለሁ፣
የመጣው ቢመጣ፤
ልበ ሙሉ አርገኸኛል፣
መንፈሰ ጠንካራ።
ትቼዋለሁ በ’ጆችህ፤
ፍረደኝ ዳኛዬ።
አውቃለሁ፣ አላፍርም፤
አንተን አቤት ብዬ።
ፍትሕ አይገኝ ከሰው፤
ፍትሕ፣ ፍትሕ ካንተ ነው።
ይምጣ፣ ይምጣ መንግሥትህ፤
ከሥቃይ ገላግሎ፣ ያስፍንልን ፍትሕ።
ትቼዋለሁ በ’ጆችህ፤
ፍረደኝ ዳኛዬ።
አውቃለሁ፣ አላፍርም፤
አንተን አቤት ብዬ።
የእስር ቤት ግድግዳ እንኳ የዚህን ወጣት ተስፋ አላደበዘዘበትም።
ወንድማችን ጥላቻ እንዲያድርበት
በሚያደርጉ ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ
በዓይነ ሕሊናው እምነቱን የሚገነቡ ነገሮችን ማየቱ ጠቅሞታል።
ሲያገለግል፣ ሲሰበሰብና ከወንድሞች ጋር ሲጫወት
በዓይነ ሕሊናው ተመልክቷል።
ከዚህ ፕሮግራም በሚቀጥሉት ቀናት ወይም ሳምንታት
የሚያበረታቷችሁ ምን ነጥቦች አገኛችሁ?
ስሜታችንን ከሚያሟጥጡ ነገሮች በመራቅ
ኃይላችንን በጥበብ መጠቀም እንዳለብን ተምረናል።
ይህን ማድረግ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ ሌሎችን መርዳት ነው።
አንዳንዶች ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ሲሉ
ፕሮግራማቸውን በማመቻቸት
በአገልግሎታቸው ይበልጥ ደስተኞች የሆኑት እንዴት እንደሆነ ተመልክተናል።
የዮናስን መጽሐፍ በጥልቀት በመመርመርም ብዙ ትምህርቶች አግኝተናል።
በዚህ ወር ሰላምታ ይዘንላችሁ የመጣነው ከሞንቴኔግሮ ነው።
ሞንቴኔግሮ የሚለው ስም በቬንስ ጣልያንኛ ጥቁር ተራራ ማለት ነው።
ስያሜው የተገኘው የአገሪቱ ተራሮች
ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች ስለ ተሸፈኑ ሳይሆን አይቀርም።
ስሟ ውስጥ ካለው መግለጫ በተቃራኒ ሞንቴኔግሮ
አድሪያቲክ ባሕር ላይ ባሉ ዓይን በሚስቡ ማራኪ የባሕር ዳርቻዎችና
በተለያዩ እንስሳዎች የተሞላች ናት።
ታራ ሪቨር ካንየን አውሮፓ ውስጥ ካሉ ጥልቅ ሸለቆዎች መካከል አንዱ ነው።
የስኩትሪ ሐይቅ ባልካን ውስጥ ካሉት ሐይቆች መካከል ትልቁ ነው።
በዚህ ሐይቅ ላይ ወደ 280 የሚያህሉ የወፍ ዝርያዎች አሉ።
ብዙዎች ጥንታዊቷን የኮቶርን ከተማ ይጎበኛሉ።
የከተማዋን ማራኪ እይታና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ይወዷቸዋል።
ታዋቂ በሆኑት ጠመዝማዛ መንገዶቿ ላይም ሳይክል ይነዳሉ።
ዘመናዊው የሞንቴኔግሮ ታሪክ በጦርነትና በሥቃይ የተሞላ ነው።
የሰርብ፣ የክሮአትና የስሎቬን መንግሥት
1918 ሞንቴኔግሮን የግዛቱ አካል አደረጋት።
በ1929 ይህ መንግሥት ስሙን ቀይሮ የዩጎዝላቪያ መንግሥት ተባለ።
የዚህ መንግሥት ግዛቶች በአሁኑ ወቅት
ቦስኒያና ሄርዘጎቪና፣ ክሮኤሺያ፣ ኮሶቮ፣ ሰሜን መቄዶንያ፣ ሞንቴኔግሮ፣
ሰርቢያና ስሎቬንያ የሚባሉትን አካባቢዎች ይጨምራል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ደግሞ
ሶሻሊስት ዩጎዝላቪያ ተመሠረተች።
ዩጎዝላቪያ በ1992 ተበታትናለች።
ሞንቴኔግሮ በ2006 ከሰርቢያ ተገነጠለች።
የሞንቴኔግሮ ሕዝቦች ያሳለፉት ከባድ ጊዜ
በርካታ ግሩም ባሕርያትን እንዲያፈሩ አስችሏቸዋል።
ካዳበሯቸው ባሕርያት መካከል ጽናት፣ ትሕትና፣
የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግና ሌሎችን ማክበር ይገኙበታል።
በ1920 ፍራንስ በርናንድ የተባለ ሰርቢያዊ ወጣት
ኦስትሪያ ውስጥ አንድ ንግግር አዳምጦ እውነትን ሰማ።
ግን ብዙም ሳይቆይ በተቃዋሚዎች ረብሻ ምክንያት ንግግሩ ተቋረጠ።
እዚያ ንግግር ላይ የሰማውን ነገር ያልረሳው ፍራንስ
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመስበክ ወሰነ።
ወደ ትውልድ መንደሩ ሲመለስ ከሌሎች ሰዎች ሆኖ
መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ጀመረ።
ከጊዜ በኋላ ወደ ማሪቦር ስሎቬንያ ሄደ።
በዚያም ጸጉር አስተካካይ ሆኖ እየሠራ ለደንበኞቹ መመሥከር ጀመረ።
ደንበኞቹ በጥሞና ያዳምጡት ነበር።
በሌላ ቦታ ደግሞ አልፍሬድ ቱቼክ የተባለ የንጉሣዊ ዘብ ኦርኬስትራ መሪ
በሥራ ባልደረባው አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ደረሰው።
ጥሩ ክፍያ የሚያስገኝለትን የወታደራዊ ሙዚቃ መሪነት ሥራውን ትቶ
በቀድሞ ዩጎዝላቪያ ከነበሩት የመጀመሪያዎቹ አቅኚዎች መካከል አንዱ ሆነ።
በ1930ዎቹ መጀመሪያ ከሌሎች ወንድሞች ጋር እየተጓዘ
የፍጥረት ፎቶ ድራማን ማሳየት ጀመረ።
ከሚስቱ ከፍሪዳ ጋርም ዛሬ ክሮኤሽያ፣ መቄዶንያ፣
ሞንቴኔግሮና ሰርቢያ በሚባሉት አካባቢዎች አገልግሏል።
ለአገልግሎት ሳይክልና ሞተርሳይክል ይጠቀሙ ነበር።
ዛሬም በሞንቴኔግሮ ያሉት 432 አስፋፊዎች በቅንዓት እየሰበኩ ነው።
የአስፋፊዎች ቁጥር ከ2024 አራት በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን
አንድ ሦስተኛ የሚያህሉት አቅኚዎች ናቸው።
በሰሜንና በደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉት መልክዓ ምድሮች የተለያዩ ናቸው።
አስፋፊዎች የሚሰብኩበትም መንገድ እንደዚያው!
ለምሳሌ የሞንቴኔግሮ ዋና ከተማ በሆነችው በፖድጎሪትሳ የሚገኘው
የፖድጎሪትሳ ሰሜን ጉባኤ የአገልግሎት ክልሉ በጣም ሰፊ ነው።
አንዳንድ አስፋፊዎች የሚኖሩት
ከስብሰባ አዳራሹ 100 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀው ስለሆነ
እዚያ ለመድረስ ሁለት ሰዓት ያህል ይጓዛሉ።
በጉባኤው የሚገኙት አስፋፊዎች
ራቅ ባሉት መንደሮች ውስጥ ከሚገኙ ወንድሞች ጋር ለመስበክ
በወር አንዴ ወይም ሁለቴ የስብከት ዘመቻ ያዘጋጃሉ።
በተቻለ መጠን ለብዙዎች ለመስበክ ጥረት ያደርጋሉ።
ቀናቸውን የሚጀምሩት መናፈሻ ውስጥ የስምሪት ስብሰባ በማድረግ ነው።
ከዚያ ያገለግላሉ፤
እንዲሁም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት የጉባኤ ስብሰባ ያደርጋሉ።
ምሽቱን በዚያ በሚገኙ ወንድሞች ቤት ካሳለፉ በኋላ
በማግስቱ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ።
ደቡባዊው የአገሪቱ ክፍል ደግሞ
ውብ የሆኑ የባሕር ዳርቻዎች አሉት።
አንዳንድ ጊዜ የጎብኚዎች ቁጥር
ከአካባቢው ነዋሪዎች ቁጥር በእጥፍ ይበልጣል።
ጎብኚዎች በሚበዙበት ወቅት
ጉባኤዎች በአደባባይ ምሥክርነት ላይ ያተኩራሉ።
በሌሎች ወቅቶች ደግሞ ከቤት ወደ ቤትና
በንግድ አካባቢዎች ይሰብካሉ።
ጥረታቸውም ፍሬ አፍርቷል።
በ2024 በመታሰቢያው በዓል ላይ 769 ሰዎች ተገኝተዋል።
በኸርዚግ ኖቪ የሚገኙ 37 አስፋፊዎች
በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ወንድሞችና እህቶች
ሞቅ ያለ ፍቅራዊ ሰላምታቸውን ልከዋል።
ይህ ከይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚተላለፍላችሁ
JW ብሮድካስቲንግ ነው።