JW subtitle extractor

JW ብሮድካስቲንግ—ግንቦት 2026

Video Other languages Share text Share link Show times

ለJW ብሮድካስቲንግ እንኳን ደህና መጣችሁ!
አምላካችን ይሖዋ ምን ዓይነት አባት ነው?
በዚህ ወር ፕሮግራማችን የይሖዋ ቤተሰብ አባል መሆን
ጥበቃና ደህንነት የሚያስገኝልን እንዴት እንደሆነ እናያለን።
በሕይወቷ ያልጠበቀችው መጥፎ ዜናና መከራ ቢያጋጥማትም
ለአባቷ ለይሖዋ ታማኝ የሆነችን እህት ተሞክሮ እንሰማለን።
ውድ ሀብት ለማግኘት ቆፍሩ በሚለው ዓምድ ሥር
የናሆምን መጽሐፍ እንመረምራለን።
በተጨማሪም በዚህ ወር ፕሮግራማችን ሁለት አዳዲስ ዓምዶች ይቀርቡልናል።
በመጀመሪያው ዓምድ ላይ ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ራሳችንን ስናቀርብ
ይሖዋ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ እንዴት እንደሚያሠለጥነን እናያለን።
በሁለተኛው ዓምድ ላይ ደግሞ
በተለያዩ ምድቦች የሚሠሩ ወንድሞችና እህቶች ሕይወት ምን እንደሚመስል እናያለን።
ይህ JW ብሮድካስቲንግ ነው።
አባት የሚለውን ቃል ስትሰሙ ወደ አእምሯችሁ ምን ይመጣል?
ለቤተሰቡ በጥልቅ የሚያስብ አፍቃሪና ሩኅሩኅ ሰው?
ወይም ለቤተሰቡ ጊዜ የማይሰጥ ግዴለሽ ምናልባትም ጨካኝ የሆነ ሰው?
የሚሰማን ስሜት አባታችን ባለው ወይም በነበረው ባሕርይ ላይ የተመካ ነው።
ግን “አባት” ስለሚለው ቃል መወያየት ያስፈለገን ለምን ነው?
አንዱ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን አባት ብሎ ስለሚጠራው ነው።
እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ መጠሪያዎች ተገልጿል።
ሆኖም ኢየሱስ አባት የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ መጠቀሙ
ይሖዋ በአገልጋዮቹ ዘንድ እንዴት መታወቅ እንደሚፈልግ ያሳያል።
በተመሳሳይም ኢየሱስ በተለያዩ የማዕረግ ስሞች ተጠርቷል።
ዋና ሠራተኛ፣ ቃል፣ የመላእክት አለቃ ሚካኤል።
ግን በዋነኝነት የሚታወቀው “የይሖዋ ልጅ” ተብሎ ነው።
በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነትም
ይሖዋ ፍጽምና የጎደለንን እኛንም “ልጆቼ” ብሎ ይጠራናል።
ይሖዋ ከእኛ ጋር የጠበቀ የአባትና የልጅ ግንኙነት እንዲኖረው ይፈልጋል።
አባት የሚለው ቃል ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ያለውን ስሜት ያሳያል።
ይሖዋ ለቤተሰብ ዝግጅት ፍቅር አለው።
ነብዩ ኢሳይያስ በኢሳይያስ 64:8 ላይ
ይህንን እንዴት እንደገለጸው ልብ እንበል፦
“አሁን ግን ይሖዋ ሆይ፣ አንተ አባታችን ነህ።
እኛ ሸክላ ነን፤ አንተም ሠሪያችን ነህ፤ ሁላችንም የእጅህ ሥራ ነን።”
እንዴት ደስ የሚል አገላለጽ ነው!
“ይሖዋ ሆይ፣ አንተ አባታችን ነህ።”
ሰብዓዊ አባታችን ያለው ባሕርይ ጥሩም ይሁን መጥፎ
አምላካችን ይሖዋ ግሩም አባት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች ላይ ይሖዋ ምን ዓይነት አባት እንደሆነ ይነግረናል።
የሚገርመው ኢየሱስ በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ ብቻ
አባት የሚለውን ቃል ከ160 ጊዜ በላይ ጠቅሷል።
ብዙ ነው አይደል?
ነጥቡ ምንድን ነው?
እኛ ለይሖዋ ቤተሰቡ ነን።
ይሖዋ ምን ዓይነት አባት እንደሆነ ይበልጥ ባወቅን መጠን
ባሕርያቱንና ለእኛ ያለውን ፍቅር እንገነዘባለን።
ይበልጥ እንድንወደውና እንድንታመንበት፣
እንደ አባታችን እንድናየው ያደርገናል።
ይህን በአእምሯችን ይዘን
ከይሖዋ ጋር ዝምድና መመሥረት የቻልንበት ምክንያት እንመርምር።
እስቲ የዘፍጥረት ምራፍ 1፡26ን የመጀመሪያውን ክፍል እናንበብ።
እዚህ ላይ ይሖዋ በምድር ላይ ስለሚኖሩት ልጆቹ አፈጣጠር
ከኢየሱስ ጋር እየተወያየ ነው።
“ከዚያም አምላክ ሰውን በመልካችን እንደ አምሳላችን እንሥራ” አለ።
ይሖዋን የምንመስልባቸው ብዙ ነገሮች አሉ።
ይህ የሚያስገርም አይደለም።
ምክንያቱም ልጆች በአብዛኛው ወላጆቻቸውን ይመስላሉ።
ታዲያ ይሖዋ አምላክን የምንመስልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
በአካላዊ ሁኔታችን አንመሳሰልም።
ምክንያቱም ይሖዋ መንፈስ ነው።
የምንመሳሰልበትን መንገድ 1 ዮሐንስ 4:8 ፍንጭ ይሰጠናል።
“ፍቅር የማያሳይ አምላክን አያውቅም።”
ለምን?
“ምክንያቱም አምላክ ፍቅር ነው።”
በአምላክ አምሳል ስለተፈጠርን የእሱን ባሕርያት ማንጸባረቅ እንችላለን።
ስለዚህ ዋነኛ ባሕርይው የሆነውን ፍቅርን ማንጸባረቅ እንችላለን።
ይሖዋ ቤተሰቡን የሚወድ አፍቃሪና ተንከባካቢ አባት ነው።
እኛም በእሱ አምሳል የተፈጠረን ልጆቹ ነን።
ስለዚህ እሱን መውደድ እንችላለን።
እንደሚወደንም እርግጠኞች ነን።
አዎ፣ ከይሖዋ ጋር ላለን ዝምድና መሠረቱ ፍቅር ነው።
ይሖዋ በሦስት መንገዶች ለልጆቹ ያለውን ፍቅር ገልጿል።
እስቲ እንመልከታቸው።
አንደኛ፣ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት ይሖዋ ያስብልናል።
አንደኛ ጴጥሮስ 5:7 ላይ እንዲህ ተብለናል፦
“የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤
ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።”
ለአንድ ሰው አሳቢነት ማሳየት ቁሳዊ ፍላጎቶቹን ማሟላትን ይጨምራል።
ይህም ጥሩ ነገር ነው።
ግን ይሖዋ አሳቢነት የሚያሳየን ቁሳዊ ፍላጎታችንን በማሟላት ብቻ ነው?
በፍጹም!
ሁለተኛ ቆሮንቶስ 1፡3, 4 ምን እንደሚል ልብ በሉ፦
“የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው
“የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይወደስ፤ . . .
እሱ በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል።”
አስተዋላችሁ?
ይሖዋ የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ ነው።
አዎ፣ ይሖዋ የሚያስፈልገንን ቁሳዊ ነገሮች ያሟላልናል።
ሆኖም ከዛም በላይ ያደርግልናል።
ይሖዋ ለስሜታችን ይጠነቀቅልናል።
ያስብልናል።
እንዲሁም ያጽናናናል።
ይሖዋ አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶቻችንን ያሟላልናል።
ለምሳሌ፣ መጠነኛ ጉዳት አጋጥሟችሁ ሐኪም ቤት ሄዳችሁ እንበል።
ዶክተሩ ሕክምና እንደሚያስፈልጋችሁ ነገራችሁ።
የቅርብ ክትትል በማድረግ እንደሚንከባከባችሁ ነገራችሁ።
ግን ሕክምና የሚያደርግላችሁ ሰው
ልምድ ያለው ሐኪም ብቻ ሳይሆን አባታችሁ ቢሆንስ?
አሁን አባታችሁ ቅድሚያ የሚሰጠው እናንተን ለመንከባከብ ነው።
ስለዚህ እናንተን ማከም ብቻ ሳይሆን
በየቀኑ ትኩረት ሰጥቶ ይንከባከባችኋል።
ይህ ያጽናናችኋል።
አባታችን ስለሆነ በፍቅር ይንከባከበናል።
ይሖዋም እንዲህ ዓይነት አባት ነው።
ይሖዋ የተዋጣለት ሐኪም ነው።
ሥቃይና መከራን የሚያስወግድበትንም ጊዜ ወስኗል።
ይህ ብቻ ግን አይደለም።
ይሖዋ የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ ነው።
በግለሰብ ደረጃ ያስብልናል፤
እንዲሁም ይንከባከበናል።
ይህን የሚያደርገው ይህ ሥርዓት ከመደምደሙ በፊት ብቻ ሳይሆን
ከተደመደመ በኋላም ነው።
የይሖዋን ፍቅራዊን እንክብካቤና ማጽናኛ በሕይወታችሁ ተመልክታችኋል?
የእሱን ፍቅርና ምሕረት በሚያንጸባርቁ
በጉባኤ የሚገኙ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ተጠቅሞ
ፍቅራዊ እንክብካቤ አድርጎላችሁ ይሆናል።
ወይም ደግሞ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በመጠቀም
አበረታቷችሁ ወይም አጽናንቷችሁ ይሆናል።
አልያም ያነበባችሁት አንድ ጥቅስ
ይሖዋ ስለሰጠው ተስፋ አዲስ ግንዛቤ አስጨብጧችሁ ይሆናል።
ይሖዋ የሚያስብልን እኛን ስለሚወደን ነው።
ፍቅሩ ዘላለማዊ ስለሆነ ለዘላለም ይንከባከበናል።
ሁለተኛው ይሖዋ አፍቃሪ አባት መሆኑን ያሳየበት መንገድ
የልባችንን አውጥተን ለእሱ እንድንነግረው መፍቀዱ ነው።
ግልጽ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ቤተሰብ ደስተኛ እንዲሆን ወሳኝ ነገር ነው።
ብዙ ቤተሰቦች በራት ሰዓት ተሰብሰበው ስለውሏቸው ማውራት ያስደስታቸዋል።
ቅድም ያነበብነው 1 ጴጥሮስ 5 ላይ
ይሖዋ ‘የሚያስጨንቀንን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ እንድንጥለው’ ጋብዞናል።
ይሖዋ ያለው በሰማይ ነው።
ታዲያ ከእሱ ጋር የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
በጸሎት አማካኝነት!
ጸሎት ለይሖዋ ስለሚያሳስቡን፣ ስለሚያስጨንቁን፣
ስለምንደሰትበት፣ ስለ ግባችን ለእሱ የመንገር አጋጣሚ ይሰጠናል።
እንዲሁም እሱን ለማመስገን ያስችለናል።
አንድ አፍቃሪ አባት ልጆቹን እንደሚያዳምጥ ሁሉ
ይሖዋም ጸሎታችንን ይሰማል።
ግን ይሖዋ ጸሎታችንን ከመስማት ያለፈ ነገር ያደርጋል።
ለጸሎታችን መልስ ይሰጠናል።
ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን በመንፈሱ በመምራት
የእሱን ሐሳብ እንድናውቅ አስችሎናል።
መጽሐፍ ቅዱስንና ባሪያው የሚያዘጋጃቸውን መንፈሳዊ ጽሑፎች
ስናነብና ስናሰላስል
ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን ተጠቅሞ
አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ እንድናተኩር ያደርጋል።
አስተሳሰባችን በእሱ አስተሳሰብ እንዲቃኝ ያደርጋል።
ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ለመስጠት አገልጋዮችን
ወይም አገልጋዮቹ ያልሆኑ ሰዎችን ሊጠቀም ይችላል።
ለጸሎታችን መልስ የሰጠን እንዴት እንደሆነ በንቃት መከታተል አለብን።
የሰጠንን መልስ በዝርዝር ጽፈን መከለስም እንችላለን።
አንዳንዴ ጸሎታችን መልስ እስኪያገኝ
የተወሰነ ጊዜ መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው?
ያለንበት ሁኔታ ይሖዋን ስላላሳሰበው ወይም
ለሌሎች ሰዎች የጸሎት ቅድሚያ ስለሰጠ ነው?
እንደዛ ማለት አይደለም።
መልሱን በትዕግሥት መጠበቅ ስላለብን ሊሆን ይችላል።
ወይም ጸሎታችን የተመለሰው
እኛ በጠበቅነው መንገድ ስላልሆነ ሊሆን ይችላል።
አንድ ባልና ሚስት ልጆቻቸውን አያቶቻቸው ጋር እየወሰዷቸው ነው እንበል።
ጉዞው አሥር ሰዓት እንደሚወስድ ወላጆቹ ያውቃሉ።
ሆኖም ልጆቹ መጀመሪያ የሚጠይቁት ምንድን ነው?
“አሁንም ገና አልደረስንም?”
ልጆቹ አያቶቻቸው ቤት ቶሎ መድረስ ይፈልጋሉ።
ምን ያህል ደጋግመው ቢጠይቁ ጉዞ የሚፈጀው አሥር ሰዓት ነው።
ግን መድረሳቸው አይቀርም።
በጉዞው ወቅት መታገሥና አእምሯቸውን በሌላ ነገር ማስጠመድ ይኖርባቸዋል።
እኛም የዚህ ሥርዓት መጨረሻ እንዲመጣ እንጸልያለን።
እውነቱን ለመናገር መጨረሻው ዛሬ ቢሆን ይለናል።
እኛም እንደ ልጆቹ ይሖዋን
“አሁንም ገና አልደረስንም?” እንለው ይሆናል።
መጨረሻው እንዲመጣ መጸለያችን ተገቢ ነው።
ሆኖም በጉዞ ላይ እንዳሉት ልጆች
የጸሎታችንን መልስ ለማግኘት በትዕግሥት መጠበቅ አለብን።
ልጆቹ መታገሥ ቢኖርባቸውም በጉዟቸው ላይ ብቻቸውን አይደሉም።
ወላጆቻቸው አሉ።
በተመሳሳይም በትዕግሥት መጠበቅ ቢኖርብንም
በምናደገው ጉዞ ሁሉ ይሖዋ ከጎናችን አይለይም።
ይህ ሥርዓት ይሖዋ በወሰነው ጊዜ ይደመደማል።
እኛ በይሖዋ ሥራ የምንጠመድ ከሆነ ግን ጊዜው ሳይታወቀን ሊያልፍ ይችላል።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ይሖዋ ለጠየቅነው ነገር የሚሰጠን ምላሽ
“አይ፣ አይሆንም” የሚል ሊሆን ይችላል።
አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው የሚጠይቋቸውን ነገሮች ሁሉ
ዝም ብለው አይሰጧቸውም።
ሐዋርያው ጳውሎስን አስታውሱ።
ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ ብሎ የገለጸው አንድ ችግር ነበረበት።
እስቲ አስቡት፦
ይሖዋ ለጳውሎስ ሌሎችን የመፈወስ ችሎታ ሰጥቶት ነበር።
ሆኖም ጳውሎስ ይህ የሥጋ መወጊያ እንዲወገድለት ሶስት ጊዜ ለምኗል።
ያገኘው መልስ ግን “አይሆንም” የሚል ነው።
ይሖዋ ለጳውሎስ ጸሎት የሰጠው መልስ “ጸጋዬ ይበቃሃል” የሚል ነው።
የሥጋ መወጊያውን አላስወገደለትም።
ሆኖም ይሖዋ የሥጋ መወጊያውን መቋቋም የሚችልበት ኃይል እንደሚሰጠው ቃል ገብቶለታል።
ይሖዋ ለእኛም መከራዎችን እንድንቋቋም ኃይል ይሰጠናል።
መከራዎችን በጽናት በመቋቋም ለአባታችን ለይሖዋን ያለንን ፍቅር ማሳየት እንችላለን።
የጸሎታችንን መልስ በትዕግሥት ስንጠባበቅም ይሁን ወይም እንደ ጳውሎስ አይሆንም የሚል ምላሽ ብናገኝም ይሖዋ ግን እንደሚወደን እርግጠኞች ነን።
ሐዋርያው ዮሐንስ በይሖዋ መንፈስ ተገፋፍቶ በዮሐንስ 14፡21 ላይ የጻፈውን እስቲ አብረን እናንብበው።
እዚህ ላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እኔን የሚወደኝ ትእዛዛቴን የሚቀበልና የሚጠብቅ ነው።”
ቀጥሎ ምን እንዳለ ልብ በሉ፦ “እኔን የሚወደኝን ሁሉ ደግሞ አባቴ ይወደዋል።”
ይሖዋ “በሙሉ አቅማችሁ የኢየሱስን ምሳሌ ከተከተላችሁ እወዳችኋለሁ” እያለን ነው።
ይሖዋ “እወዳችኋለሁ” ሲለን ደግሞ ከልቡ ነው።
ከአፍቃሪ አባታችን ከይሖዋ ጋር በነፃነት መነጋገር መቻላችን ትልቅ መብት እንደሆነ ጥርጥር የለውም።
ይሖዋ አፍቃሪ አባት መሆኑን ያሳየበትን ሦስተኛውን መንገድ እስቲ እንመልከት፦ ቤተሰቡን ለመንከባከብ የሚያስፈልገውን ሁሉ ያደርጋል!
ልጆችን ማሳደግ አስደሳች ነገር ነው።
ግን ለየትኛውም ወላጅ ቢሆን ቀላል ሥራ አይደለም።
ልጆቹ ጥሩ ባሕርይ ቢኖራቸው እንኳ ይህን እውነታ አይቀይረውም።
ሁላችንም ልጆች እያለን ወላጆቻችንን አስቸግረን እናውቃለን።
እስቲ ወላጆች ለልጆቻቸው ከሚያደርጓቸው ነገሮች ጥቂቶቹን እናንሳ።
ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያ ማቅረብ፣
እንዲሁም ዘና የሚሉበትን ሁኔታ መፍጠር።
ሲያማቸው ወደ ሐኪም ቤት መውሰድ፣ ማስተማር እንዲሁም መገሠጽ።
ምን?
ተግሣጽ?
ተግሣጽን ብዙ ጊዜ የምናያይዘው ከቅጣት ጋር ነው።
እውነት ነው፣ ቅጣት የተግሣጽ አንዱ ክፍል ነው።
ተግሣጽ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ
መመሪያን፣ ትምህርትን፣ ሥልጠናን እንዲሁም
እርማት መስጠትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ደግሞም ተግሣጽ ጥሩ ነገር ነው።
ተግሣጽ ትምህርትና ሥልጠና ከመስጠት ጋር አብሮ የሚሄድ ነው።
ይሖዋ ለዘላለም በደስታ እንድንኖር ስለሚፈልግ አንዳንዴ ይገሥጸናል።
ይሖዋ ይገሥጸናል ስንል ምን ማለታችን ነው?
ይሖዋ በመንፈሳዊ ማደግ እንድንችን ይመራናል፣ ያስተምረናል፣
ያሠለጥነናል እንዲሁም እርማት ይሰጠናል ማለታችን ነው።
ይህን የሚያደርገው በቃሉ፣
ታማኝና ልባም ባሪያ በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች
እንዲሁም በጎለመሱ ክርስቲያኖች አማካኝነት ነው።
በዚህ መንገድ መንፈሳዊ ክህሎት እንድናዳብር ይረዳናል።
ጥሩ ወላጅ መሆን ጠንክሮ መሥራት ይጠይቃል።
እናንተ ወላጆችም ይህን በደስታ እያከናወናችሁ ነው።
ይሖዋም ጥረታችሁን ከፍ አድርጎ ይመለከታል።
እሱም ቢሆን ብዙ ነገር ያደርጋል።
ለእኛ ሲል!
እንዲያውም እንደ አንድ አፍቃሪ አባት
እኛን ለመርዳት ለብዙ ሺህ ዓመታት የተለዩ ነገሮችን አድርጓል።
እስቲ ስለሚያስደስቷችሁ የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ለማሰብ ሞክሩ፦
ፀሐይ ስትጠልቅ ማየት፣ ጣፋጭ ምግብ መመገብ፣ አስደሳች ዝማሬ መስማት።
የአበቦች መዓዛ፣ ከወዳጅ ዘመድ ጋር አብሮ መሆን
እንዲሁም እምነታችንን የሚያጠናክሩ ዝግጅቶች።
እነዚህን ሁሉ መልካም ነገሮች ያገኘነው ከአፍቃሪው አባታችን ከይሖዋ ነው።
ይሖዋ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ሁሉ ያሟላል።
ይህን የሚያደርገው ስለሚወደን ነው።
በመግቢያችን ላይ አንድ ጥያቄ አንስተን ነበር፦
አባት የሚለውን ቃል ስትሰሙ ወደ አእምሯችሁ ምን ይመጣል?
የምንሰጠው መልስ ወላጅ አባታችን እኛን እንዳያዘበት ሁኔታ ይለያያል።
ምናልባት ያደጋችሁት ያለ አባት ቢሆንስ?
ይሖዋ ለእናንተ ያለውን ፍቅር
በመዝሙር 68፡5 ላይ እንዴት እንደገለጸው ተመልከቱ፦
“በተቀደሰ መኖሪያው ያለው አምላክ
አባት ለሌላቸው ልጆች አባት፣ ለመበለቶች ደግሞ ጠባቂ ነው።”
በሰማይ ካለው የተቀደሰ መኖሪያው ሆኖ
እናንተ ያላችሁበትን ሁኔታ ይመለከታል።
ውድ የቤተሰቡ አባል እንደሆናችሁ ይሖዋ ማረጋገጫ ሰጥቷችኋል።
ጥቅሱ ምን እንዳለ ልብ በሉ፦
“አምላክ አባት ለሌላቸው ልጆች አባት፣
ለመበለቶች ደግሞ ጠባቂ ነው።”
በሌላ አባባል ይሖዋ እንዲህ እያላችሁ ነው፦
‘ይህ የማንነቴ አንዱ ገጽታ ነው።
‘አባት ባይኖራችሁ ወይም የእሱን ድጋፍ ባታገኙ
‘እኔ አለሁላችሁ።
እኔ አባታችሁ ነኝ።’
ግን አባታችሁ ወይም ቤተሰባችሁ
ይሖዋን በማምለካችሁ ምክንያት የሚቃወሟችሁ ቢሆኑስ?
በማርቆስ ምዕራፍ 10፡29, 30 ላይ የተሰጣችሁን ተስፋ ልብ በሉ።
ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦
“እውነት እላችኋለሁ፣ ስለ እኔና ስለ ምሥራቹ ሲል ቤትን ወይም ወንድሞችን
“ወይም እህቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ፣
“አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እህቶችን፣ እናቶችን፣
“ልጆችንና እርሻን 100 እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛል።”
ይሖዋን በማምለካችሁ ምክንያት
ወላጆቻችሁ ወይም የቤተሰብ አባሎቻችሁ አግልለዋችኋል?
ይህን አስታውሱ፦
የይሖዋ ቤተሰብ አባል ናችሁ።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ አምላኪዎች ይወዷችኋል።
ዛሬ ይሖዋን የማያውቁት የቤተሰብ አባሎቻችሁ
አንድ ቀን ይሖዋን እንደሚያመልኩት ተስፋ አድርጉ።
ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን አገልጋዮቹ እስከሆነን ድረስ
የይሖዋ ቤተሰብ አባል መሆናችንን መቼም አንርሳ።
ይሖዋ ልጆቹን፣ አዎ ልጆቹን ምንጊዜም ይወዳቸዋል።
በቅርቡ ይህን ሥርዓት በማጥፋት
ኃጢአትና ሌሎች ችግሮች የሌሉበት
አዲስ ዓለም እንዲመጣ ያደርጋል።
እስከዛው ግን በርኅራኄ የሚያስፈልገንን ያሟላልናል።
ጸሎታችንን ያዳምጣል፤
በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ መልስ ይሰጠናል።
አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ
ቤተሰቡን ለዘላለም ሕይወት ለማብቃት ብዙ ነገር እያደረገ ነው።
ቤተሰቡን በጣም ስለሚወድ ከዚህም በላይ ያደርጋል።
ይሖዋ ለቤተሰቡ ሲል የማይሆነው ነገር የለም።
ለዚህ ሁሉ ይሖዋን እናመሰግናለን።
ኢሳይያስ በተናገረው ሐሳብም እንስማማለን።
“ይሖዋ ሆይ፣ አንተ አባታችን ነህ።”
እህት ቤቴል ሮዲሽ 22 ዓመት ሲሆናት
በብሩክሊን ቤቴል የማገልገል ዕቅድ ነበራት።
ግን የአንጎል ዕጢ እንዳለባት ስታውቅ ዕቅዷ ተቀየረ።
ተሞክሮዋ የሚያዝያ 22, 1990 ንቁ! ላይ ወጥቷል።
ከዚያን ጊዜ አንስቶ
እህት ቤቴል ይሖዋ በእርግጥ አባቷ መሆኑን
በግልጽ የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎችን አግኝታለች።
አንድ ቀን ጠዋት ብሩክሊን ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ስልክ ተደውሎ
በጊዜያዊነት ለሦስት ወር እንዳገለግል ግብዣ ቀረበልኝ።
ግን የሐኪም ቀጠሮ ስለነበረብኝ
ብዙም ሳናወራ ወንድምን ቅርታ ጠየቄ ስልኩ ተዘጋ።
ዶክተሩ የምርመራው ውጤት ጨንቅላቴ ውስጥ
ትልቅ ዕጢ መኖሩ እንደሚያሳይ ነገረኝ።
ስለዚህ ‘ቤተሰቦችሽ መምጣት ይኖርባቸዋል’ አለኝ።
ዕጢውን ለማውጣት ሁለት ጊዜ ቀዶ ሕክምና ማድረግ አስፈልጎኛል።
ቀዶ ሕክምናውን ያደረገልኝ ዶክተር በጣም ጎበዝ ዶክተር ነበር።
ከሁለተኛው ቀዶ ሕክምና በኋላ ዶክተሩ ደስ የሚል ዜና ነገረን።
ዕጢው ከጨንቅላቴ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወጥቷል።
በአንድ ዓመት ውስጥ ሕይወቴ ወደ ቀድሞው ተመለሰ።
በ1990 መጀመሪያ አካባቢ ብሩክሊን ውስጥ መኖር ጀመርኩ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ቤቴል ከሚያገለግለው ከቦብ ሮዲሽ ጋር ተዋወቅን።
ከተጋባን በኋላ በቤቴል ለማገልገል አመለከትን።
እንደተፈቀደልን ሲነገረን በጣም ነው ደስ ያለን።
ከሁለት ዓመታት ገደማ በኋላ ግን አረገዝኩ።
ሴት ልጅ ወለድን።
ከዚያ ደግሞ ወንድ ልጅ ደገምን።
የሚያማምሩ ልጆች አገኘን።
ከዚህም ለሦስተኛ ጊዜ አረገዝኩ።
ግን የሚያሳዝን ነገር አጋጠመን።
ከሦስት ወር ገደማ በኋላ ልጃችን ሆዴ ውስጥ ሞተ።
ሆስፒታል እያለን ልጆቻችንን ትንከባከብልን የነበረችው እናቴ ነበረች።
ለልጆቻችን ልጅ ይዤ እንደማልመጣ ቀድማ ስለነገረቻቸው በጣም አመስጋኝ ነኝ።
ምክንያቱም ከሆስፒታል ወደ ቤት ስንመለስ በጣም ተረብሼ ነበር።
ከልጆቹ ጋር ማውራት እንኳን አልቻልኩም።
ቦብ ግን ሁሉችንም እቅፍ አድርጎ ልጁ እንደሞተ ነገራቸው።
ከልጆቹ ባሕርይና ከተፈጠረው ነገር አንጻር የተሻለ የሚሆነው
ስለ ሁኔታው ቀስ ብለን ግን በግልጽ መንገሩ እንደሆነ ተሰማን።
ለልጆቹ እንዲህ ያሉ አሳዛኝ ነገሮች እንደሚያጋጥሙ መንገራችን
እንደ ቤተሰብ ለመጽናናት ረድቶናል።
ወደ መኝታ ቤት ስገባ ለልጃችን ያዘጋጀናቸውን ልብሶች ማየት
በጣም ከባድ ነበር።
‘አሁን እዚህን ትንንሽ ልብሶች ምን ላደርጋቸው ነው?’ ብዬ አሰብኩ።
ከልጃችን ሞት ከአምስት ወር ገደማ በኋላ
ወደ ጉባኤ ስብሰባ ስንሄድ ልክ ወደ አዳራሹ እንደገባሁ
እንባዬን መቆጣጠር አቃተኝ።
ስለዚህ ወደ መኪናችን ተመለስኩ።
ይህንን ያስተዋሉ ሁለት ወዳጆቼ
ተከትለውኝ መጥተው መኪና ውስጥ አብረውኝ ተቀመጡ።
ስለሞተብኝ ልጅ፣ ስለ ሌሎቹም ልጆቼ ሳወራ በጥሞና አዳመጡኝ።
እጄን እያሻሹ በደንብ አዳመጡኝ።
አጽናኑኝ፤ እንዲያውም ፈገግ እንድል አደረጉኝ።
ከዚያም አብረን ተመለስን ወደ አዳራሹ ገባን።
ይሖዋ ከጎናችን አልተለየም።
በጉባኤው ውስጥ ወዳጆችን ሰጥቶናል።
ምንም ያህል ሥራ ቢበዛባቸው በየሳምንቱ አርብ ምሽት
ወደ እኛ ቤት በመምጣት አብረውን ራት ይበላሉ።
ቁጭ ብለን አስቂኝ የሆኑ ነገሮችን እናወራለን።
አዎንታዊ ነገር ላይ እናተኩራለን።
ይህ ደግሞ በሚሰማኝ ከባድ ሐዘን ላይ ብቻ እንዳላተኩርና
ያንን ብቻ እያሰብኩ እንዳልቆዝም ረድቶኛል።
የይሖዋን ፍቅር በወንድሞችና በእህቶች አማካኝነት ማየቴ
እኔም በተመሳሳይ ሁልጊዜ ለሌሎች ፍቅር እንዳሳይ አነሳስቶኛል።
ስለዚህ የጽሑፍ መልእክት ወይም ደብዳቤ በመጻፍ
ወይም በአካል በመሄድ ሌሎችን እንደምንወዳቸው
እንደምናስብላቸውና ከጎናቸው እንደሆነን ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን።
በሕይወቴ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይሖዋ ኃይል በመስጠት አበርትቶኛል።
ሁላችንም በጣም የደከምንበትና ‘በአገልግሎት መካፈል ወይም
ወደ ስብሰባዎች መሄድ አልችልም’ ብለን የምናስብበት ጊዜ ያለ ይመስለኛል።
ግን ይሖዋ በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ አካላዊ ብርታት ሰጥቶናል።
እንዲሁም የሚያስፈልገንን አእምሯዊና ስሜታዊ ጥንካሬ ሰጥቶናል።
ዘዳግም 33፡27 እውነት እንደሆነ በራሴ ሕይወት ተመልክቻለሁ።
እንዲህ ይላል፦
“አምላክ ከጥንት ጀምሮ መሸሸጊያ ነው፤
ዘላለማዊ ክንዶቹ ከበታችህ ናቸው።”
በሕይወቴ ያጋጠሙኝ ከባድ ፈተናዎች
በይሖዋ እርዳታ ልወጣው የማልችል ነገር እንደሌለ አስተምረውኛል።
ልክ እንደ እህት ቤቴል ሮዲሽ እምነትን ጨምሮ
ሌሎች ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበራችን
መከራዎችን በጽናት እንደንቋቋም ያስችለናል።
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈላችን
እነዚህን ባሕርያት እንድናዳብርም ይረዳናል።
በእነዚህ የአገልግሎት መብቶች መካፈላችን
ይበልጥ ጎልማሳ ክርስቲያኖች እንድንሆንና
ይሖዋን እንድንመስል ያስችለናል።
በዚህ ረገድ የሚረዳን አዲስ ዓምድ እንደተዘጋጀ ስናሳውቃችሁ ደስ ይለናል።
ርዕሱ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ክርስቲያናዊ ባሕርያት ለማዳበር ይረዳል የሚል ነው።
በተከታታይ የሚቀርቡት የዚህ ዓምድ ክፍሎች
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈሉትን ሁሉ
የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን ለማዳበር እንዴት እንደረዳቸው እናያለን።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ለማዳበር ይረዳልፍቅር
የሚለውን የመጀመሪያውን ክፍል ተከታተሉ።
ያደግኩት በአንዲት ትንሽ ከተማ ውስጥ ነው።
እዚያ ከተማ ውስጥ ያሉ ሰዎች ባሕላቸው፣ አስተሳሰባቸው
ነገሮችን የሚያከናውኑበት መንገድ ሁሉ ተመሳሳይ ነው።
ስለዚህ የስብሰባ አዳራሽ የግንባታ ቡድኑን ስቀላቀል
በጣም ትልቅ ለውጥ ነበር ያጋጠመኝ።
አንድ ዓይነት ባሕል ብቻ ካለበት አካባቢ ወጥቶ
የተለያየ ቋንቋ፣ ባሕልና ብሔር ካላቸው ሰዎች ጋር
የመሥራት አጋጣሚ አግኝቻለሁ።
በግንባታ ቡድኑ ውስጥ መሥራቴ ያደኩበት ባሕል
ከእኔ የተለየ ባሕልና ዘር ላላቸው ሰዎች
ፍቅር እንዳላሳይ እንቅፋት እንደሆነብኝ እንድገነዘብ ረድቶኛል።
በተወሰነ መጠንም ቢሆን ጭፍን ጥላቻ እንዳለብኝ አስተዋልኩ።
የማገለግለው በስብሰባ አዳራሽ ግንባታ ቡድን ውስጥ ነው።
ሁኔታው በጣም ደስ ይላል።
አብረን እንሠራለን፣ አብረን እንኖራለን፤
አሳዛኝ ሁኔታ ሲያጋጥመንም አብረን እናለቅሳለን።
በቃ ልክ እንደ ቤተሰብ ነን።
ግን የስብሰባ አዳራሽ ቡድኑን ስቀላቀል
የለመድኩትን ሕይወት መተው ነበረብኝ።
በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ የምቀርባቸውን ሰዎችና
አብሮ አደግ ጓደኞቼንም ትቼ መሄድ አስፈልጎኛል።
በፊት ካለሁበት ቦታ አንጻር
እዚህ ያሉ ወንድሞች የሚያሳዩኝ ፍቅር እንዳነሰ ተሰማኝ።
ሆኖም አንደኛ ቆሮንቶስ 13:4 እኔ እያሳየሁ ያለሁት
የፍቅርን አንዱን ገጽታ ብቻ እንደሆነ እንድገነዘብ ረዳኝ።
ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር ለማሳየት
ብዙ ነገር ማድረግ ይጠበቅብኝ ነበር።
የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ሳገለግል የተማርኩት ትልቁ ነገር
በተለይ ከሌላ አገር የመጣ ሰው
ፍቅርና ርኅራኄ ማሳየቱ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ነው።
አንዴ ንግግር እየሰጠሁ አንድ ወንድም ወደ ስብሰባው አርፍዶ ገባ።
ከዛ አርፍዶ መምጣቱ ሳያንሰው ቁጭ ብሎ ማንቀላፋት ጀመረ።
በጣም ጎበዝ ተናጋሪ እንዳልሆንኩ አውቃለሁ።
ግን እንዴት ያንቀላፋል?
በጣም አበሳጨኝ።
እንዲህ ብዬ ማሰቤ ግን ፍቅር እንደጎደለኝ የሚያሳይ ነበር።
ምክንያቱም ይሄ ወንድም እኮ በሳምንት ስድስት ቀን ይሠራል።
ያውም በየቀኑ ከ12-16 ሰዓት ያህል!
እውነት ቤት ውስጥ ያለ የሥጋ ዘመድ ስለሌለኝ
ወንድሞችና እህቶችን የማያቸው እንደ ቤተሰቤ ነው።
ኑሮ በጣም ከባድ ስለሆነ ወንድሞችና እህቶች እምነታቸውን ለመጠበቅ
ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባቸው።
በተቻለ መጠን ከእነሱ ጋር ቶሎ ለመቀራረብ ጥረት አደርጋለሁ።
ግን አንዳንዴ ተፈታታኝ ነው።
እኔም የምጥረውን ያህል እነሱ እንደማይቀርቡኝ ተሰማኝ።
ይሄ ደግሞ አበሳጨኝ።
‘ከእኔ ጋር መቀራረብ አይፈልጉም ማለት ነው?’ ስል
ማይክ እንዲህ ብሎ አመለካከቴን እንዳስተካክል ረዳኝ።
“አንቺም እኮ እንደ እነሱ ነሽ።
ከሰው ጋር ቶሎ የምትቀራረቢ ሰው አይደለሽም።”
በዚህ ጊዜ ገባኝ። ደግሞም እውነቱን ነው።
እህቶችን በትዕግሥትና እና በፍቅር መያዝ እንዳለብኝ ገባኝ።
እህቶቼን በደንብ ለመረዳት ከበፊቱ ይበልጥ ጥረት ማድረግ አለብኝ።
ይሖዋ ሁላችንንም እየቀረጸን ነው።
ግን በስብሰባ አዳራሽ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ መካፈሌ
ይሖዋ እኔን ለመቀረጽ የሚያደርገውን ጥረት ይበልጥ እንዳፋጠነው ይሰማኛል።
አሁን የማየው የሰዎችን የቆዳ ቀለም፣ ቋንቋቸውን
ወይም ዘራቸውን ሳይሆን ውስጣዊ ማንነታቸውን ነው።
በግንባታ ቡድን ውስጥ መሥራት ስጀምር ይሖዋ እንዲህ እንዳለኝ ነው ተሰማኝ፦
‘ሴቦ ለሌሎች ፍቅር ማሳየትና
‘እውነተኛ ፍቅር ምን ማለት እንደሆነ እንደምታውቂ ይሰማሻል።
ግን ሴቦ እውነተኛ ፍቅር ምን ማለት እንደሆነ እኔ ላሳይሽ።’
ስለዚህ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየተንቀሳቀስን ስንሠራ
ከወንድሞች ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ለመመሥረት እሞክራለሁ።
ሁለታችንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ በመሆናችን በጣም ተጠቅመናል።
ወንድሞችና እህቶችን ርኅራኄ በመያዝ
ይበልጥ ፍቅር እንድናሳይ ረድቶናል።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ወንድሞቼንና እህቶቼን
ይበልጥ እንድወዳቸው ረድቶኛል።
አብሬያቸው ብዙ ጊዜ ስለማሳልፍ
ያሉበትን ሁኔታ መረዳት አለብኝ።
ይበልጥ በተረዳኋዋቸው መጠን ይበልጥ እወዳቸዋለሁ።
ጥሩ አዳማጭ ለመሆን ጥረት ማድረጌ
ከባለቤቴ ጋር ስናወራም ሆነ በወረዳችን ውስጥ ያሉ እህቶች ሲያዋሩኝ
በትኩረት እንዳዳምጣቸው ረድቶኛል።
የወንድማማች መዋደድ ማዳበራችን
ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አስተዋላችሁ?
ጠንካራ ቤተሰባዊ ትስስር እንዲሁም
አንዳችን ለሌላው ትዕግሥትና ርኅራኄ እንዲኖረን ያደርጋል።
ይህ አዲስ ዓምድ ሁላችንም ራሳችንን
ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድናቀርብ እንደሚያበረታታን ተስፋ እናደርጋለን።
በመጀመሪያው ንግግር ላይ
ይሖዋ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት እንደሚገሥጸን ተመልክተን ነበር።
ብዙ ጊዜ ይህን የሚያደርገው ማሳሰቢያዎችን በመስጠት ነው።
በቀጣዩ የማለዳ አምልኮ ንግግር ላይ ወንድም ትሮይ ስናይደር
ለይሖዋ ማሳሰቢያዎች ትክክለኛ አመለካከት ማዳበር የምንችለው
እንዴት እንደሆነ ያብራራል።
አንድ ሰው እንዲህ ቢላችሁ ምን ይሰማችኋል?
‘ብታውቀውም አንድ ነገር ላስታውስ።’
‘ላሳስብህ የምፈልገው ነገር . . .’
‘ለማስታወስ ያህል . . .’
እንዳልሰማችሁ ትሆናላችሁ?
‘ይህንንማ አውቀዋለሁ’ ትላላችሁ?
‘ይህ አነጋገርማ የረሳሁት ነገር ያለ ያስመስላል’ ብላችሁ ቅር ይላችሁ ይሆን?
ወይም ደግሞ እንዲህ መባላችሁ
‘የሚጎድለኝ ነገር አለ ማለት ነው’ የሚል ስሜት ፈጥሮባችሁ ይሆን?
ስለ ይሖዋ ማሳሰቢያዎች ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ግን
ከዚህ በጣም የተለየ ነው።
መጽሐፍ ቅዱሳችንን መዝሙር 119 ላይ እናውጣና
የይሖዋ ማሳሰቢያዎች የሚፈጥሩብንን ስሜትና ያላቸውን ኃይል እንመልከት።
መዝሙር 119፡2, 3
እንዲህ ይላል፦
“ማሳሰቢያዎቹን የሚጠብቁ፣
“እሱን በሙሉ ልባቸው የሚፈልጉ ደስተኞች ናቸው።
“ክፉ ነገር አያደርጉም፤
በመንገዶቹ ይሄዳሉ።”
አዎ፣ የይሖዋን ማሳሰቢያዎች ተግባራዊ ስለምናደርግ ደስተኞች ነን።
ጥልቅ የማስተዋል ችሎታ ይኖረናል።
ግንዛቤያችንን ያሰፉልናል።
ታማኝ ሆነን ለመጽናት ያደረግነውን ውሳኔ ያጠናክሩልናል።
ቁጥር 3 ላይ እንደሚለው ትክክለኛውን ነገር እንድናደርግና
በይሖዋ መንገድ እንድንሄድ ይረዱናል።
መከራ በሚያጋጥመን ጊዜ የሚያጽናኑንም የይሖዋ ማሳሰቢያዎች ናቸው።
የይሖዋ ማሳሰቢያዎች በተጨናነቀ መንገድ ላይ እንደተተከሉ
የመንገድ ላይ ምልክቶች ናቸው።
በምሳሌያዊ ሁኔታ በዚህ አስጨናቂ ዓለም ውስጥ
መንገድ ይጠቁሙናል።
አካሄዳችን ትክክል መሆኑን ያረጋግጡልናል።
አንዳንዴ ደግሞ መንገድ ከሳትን
ወደ ትክክለኛው መንገድ እንድንመለስ ያሳስቡናል።
የዛሬው የዕለት ጥቅሳችን
ለዚህ ግሩም ማስረጃ ነው።
እባካችሁ መጽሐፍ ቅዱሳችንን
1 ጴጥሮስ 2፡13, 14 ላይ እናውጣና
ማሳሰቢያው ልብ ብለን እናንብበው።
“ለጌታ ብላችሁ ለሰብዓዊ ሥልጣን ሁሉ ተገዙ፦
“የበላይ ስለሆነ ለንጉሥ ተገዙ፤
“ደግሞም ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት፣
“መልካም የሚያደርጉትን ግን ለማመስገን
በእሱ የተላኩ ስለሆኑ ለገዢዎች ተገዙ።”
ይህ ለመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የተሰጠ ማሳሰቢያ ነው።
ይህ ጥቅስ ለመንግሥት በተወሰነ መጠን ቢገዙም
ገለልተኝነታቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው የሚናገር ነው።
ይሄ ለእነሱ አዲስ ነገር አይደለም።
ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት
እንዲሁም ይህን መንግሥት ስለመደገፍ የተናገረውን ሐሳብ በሚገባ ያውቃሉ።
ኢየሱስ የቄሳር የሆነውን ለቄሳር
የአምላክ የሆነውንም ለአምላክ ስጡ ብሎ እንዳስተማረም ያውቃሉ።
ሐዋርያት ከሰው ይልቅ ለአምላክ ልንታዘዝ ይገባል እንዳሉም ያውቃሉ።
ታዲያ ይህ ማሳሰቢያ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?
በጊዜው የነበረው ዓለም በፖለቲካ አመለካከት የተከፋፈለ ነበር።
ይህ ደግሞ በእነዚህ ክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ጫና ስለፈጠረባቸው
ገለልተኝነትን በተመለከተ በወቅቱ ለነበሩት ክርስቲያኖች
ማሳሰቢያ መሰጠቱ አስፈላጊ ነበር።
ይህ ማሳሰቢያ የረዳቸው እንዴት ነው?
ቁጥር 13ን እንመልከት።
“ለጌታ ብላችሁ” ይላል።
እይታቸውን ማስፋት ነበረባቸው።
ለመንግሥታት እንገዛለን ማለት
የመንግሥትን ፖሊሲና ጦርነት መደገፍ እንዳልሆነ
ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ራሱ በመረጠው ጊዜ ነገሮችን እስኪያስተካከል ድረስ
እንደሚጠብቁት የሚያሳይ መሆኑን አስታውሷቸዋል።
መንግሥትን ከመቃወም ይልቅ ትኩረታቸውን በአምላክ መንግሥት ላይ እንዲሁም
ስለሚያመጣቸው በረከቶች በመስበክ ላይ እንዲያተኩሩ ረድቷቸዋል።
ከተሰጣቸው ማሳሰቢያዎች መካከል
ይህ አንዱ ብቻ ነው።
ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ለሮም ጉባኤ የተጻፈው ደብዳቤ ደርሷቸው ነበር።
ደብዳቤው ክርስቲያኖች ለበላይ ባለሥልጣናት ከመገዛት አንጻር
እንዴት መመላሰስ እንዳለባቸው ይገልጻል።
ለቲቶ የተጻፈው ደብዳቤም በዚሁ ጊዜ አካባቢ ነው የደረሳቸው።
ይህ ደብዳቤም ቢሆን ለመንግሥት ተገዢዎች እንዲሆኑ አሳስቧቸዋል።
እነዚህ ሁሉ ማሳሰቢያዎች ክርስቲያኖች ገለልተኝነታቸውን እንዲጠብቁና
የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዲይዙ ረድቷቸዋል።
እነዚህ ማሳሰቢያዎች ሌላም ጥቅም ነበራቸው።
ምክንያቱም እነዚህ ክርስቲያኖች
ከፊታቸው ከባድ ስደት ይጠብቃቸው ነበር።
እነዚህን ማሳሰቢያዎች ተግባራዊ ካደረጉ
የይሖዋ እርዳታ አይለያቸውም።
ቁጥር 15 ላይ ይህ እንዴት እንደተገለጸ እንመልከት።
አንደኛ ጴጥሮስ 2፡13, 14 ላይ
ለሰብዓዊ ባለሥልጣናት መገዛት እንዳለባቸው ተነግሯቸው ነበር።
ቁጥር 15 “የአምላክ ፈቃድ፣ መልካም ነገር በማድረግ
“ከንቱ ንግግር የሚናገሩትን ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰዎች አፍ
ዝም እንድታሰኙ ነውና” ይላል።
አዎ፣ ለእነዚህ ማሳሰቢያዎች ትኩረት እስከሰጡ ድረስ
ይሖዋ እሱን ማምለካቸውን እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል።
እነዚህ ክርስቲያኖች ማሳሰቢያዎቹን እንደተከተሉ
ዛሬ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን።
ዛሬም ቢሆን ተመሳሳይ ሁኔታ ሲፈጠር እያየን ነው።
ለምሳሌ በአንዲት አገር ለሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን
በገለልተኝነት አቋማቸው እንዲጸኑ ማሳሰቢያ ተሰጣቸው። 
ብዙም ሳይቆይ አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ተነሳ።
ማሳሰቢያውን ተግባራዊ አደረጉ።
ገለልተኛ ሆኑ፤
ለመንግሥትም መገዛታቸውን ቀጠሉ።
ጦርነቱ ሲያበቃ መንግሥት
የአገሪቱን ሕዝብ አንድ ለማደረግ በማሰብ አዲስ ሕግ አወጣ።
ካወጣቸው ሕጎች መካከል አንደኛው ዜጎች ጋብቻቸውን ሲያስመዘግቡ
ከባንዲራ ጋር በተያያዘ እንዲያደርጉ የሚጠበቅባቸው ሥነ ሥርዓት
ወንድሞች የገለልተኝነት አቋማቸውን እንዲጥሱ የሚያደርግ ነበር።
ታዲያ ምን አደረጉ?
ወደ ባለ ሥልጣናቱ በመሄድ
በጦርነቱ ወቅት ገለልተኞች እንደነበሩ አስታወሷቸው።
ባለ ሥልጣናቱም ይህን ስለሚያውቁ አቋማቸውን አከበሩላቸው።
እንዲያውም አንደኛው “በዚሁ እንድትቀጥሉ እንፈልጋለን” አላቸው።
ብዙም ሳይቆይ መንግሥት
የገለልተኝነት አቋማቸውን የማያስጥስ
አዲስ ሕግ አወጣ።
ይህ ሁሉ የሆነው ይሖዋ የሰጣቸውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ስላደረጉ ነው።
እኛ የይሖዋ ሕዝቦች በየጊዜው ማሳሰቢያዎች ይሰጡናል።
ለምሳሌ የበላይ አካሉን ሪፖርት አስቡ።
በቅርቡ አገልግሎታችንን ስናከናውን ግብ እንድናወጣና
ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ምሥራቹን እንድንሰብክ ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል።
የተሰጠንን ማሳሰቢያ በሥራ ላይ ስናውል እንደሰታለን።
ይሖዋ ከእሱ ርቀው ለነበሩ ሰዎች ያለውን አመለካከትና
እኛም የእሱን ምሳሌ በመኮረጅ
ጥሩ አቀባበል እንድናደርግላቸው ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል።
በዚህ ረገድ ግንዛቤያችንን የሚያሰፋ ጥሩ የሆነ ማሳሰቢያ አግኝተናል።
ስለ አለባበሳችንም ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ብዙ ምርጫ ያለን ቢሆንም
አለባበሳችን ይሖዋንና አምልኮውን የሚያስከብር እንዲሆን ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል።
ለእምነታቸው ሲሉ ለታሰሩ ወንድሞችም እንድንጸልይ ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል።
በምንታሰርበት ወይም በምንሰደድበት ወቅትም
መስበካችንን እንድንቀጥል ማበረታቻ ተሰጥቶናል።
በቅርቡ ደግሞ በመጀመሪያው ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ
እኛም የገለልተኝነት አቋማችንን እንድንጠብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል።
ምክንያቱም የምንኖረው በጣም በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ነው።
ብዙዎች በፖለቲካዊና በማኅበራዊ ጉዳዮች የሚያራምዱት አቋም የተለያየ ነው።
የበላይ አካሉ ሪፖርት እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር፦
“የበላይ አካሉ እነዚህን ማሳሰቢያዎች መስጠት የፈለገው
ሰይጣን የአምላክ ሕዝቦችን አንዱን ወገን እንዲደግፉ ጫና እያደረገ ስለሆነ ነው።”
ከዚያም ጥቅሶች ለክርስቲያናዊ ሕይወት በተባለው ጽሑፍ ላይ
ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት እንድንመለከት ተነገረን።
በተለይ  መንግሥት በሚለው ሥር ያለውን!
እንዲህ ማድረግ ሐሳቡ በልባችን ሥር እንዲሰድ ያደርጋል።
ጥያቄ ለሚጠይቁን ሰዎችም መልስ ለመስጠት ያስችለናል። 
በአምላክ ሕዝቦች መካከልም አንድነት እንዲኖር ያደርጋል።
እኛ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችም ብዙ ማሳሰቢያዎች ይሰጡናል።
ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ይቅር እንድንል፣
ከግለሰቦች ጋርም ሆነ ከሌሎች ዲፓርትመንቶች ጋር አለመግባባት ሲፈጠር
ሰላምን እንድንፈልግ ማሳሰቢያዎች ይሰጡናል።
ማሳሰቢያዎቹን ስንሰማ ደስተኛ እንሆናለን።
በመካከላችንም ሰላም ይሰፍናል።
መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ እንድናነብም ማሳሰቢያ ይሰጠናል።
ለምን?
ሥራ ስለሚበዛብን!
መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ይሖዋ በየቀኑ እንዲያናግረን እንድንፈቅድ
ማሳሰቢያ ይሰጠናል።
ለበላይ ተመልካቾችም ዋነኛው ሥራችን
ለወንድሞች እረኝነት ማድረግ እንደሆነ ማሳሰቢያ ይሰጠናል።
ማሳሰቢያ የሚሰጠን ለምንድን ነው?
ምክንያቱም አንዳንዴ ሥራው ላይ ብቻ እናተኩርና
የይሖዋን በጎች ልንረሳ እንችላለን።
“አልረባም” የሚል ስሜት ሲሰማንም
ይሖዋ እንደሚወደን በማስታወስ
ይህን ስሜት እንድንታገለው ማሳሰቢያ ይሰጠናል።
ይሖዋ የሚያተኩረው መልካም ጎናችን ላይ ነው።
ምሕረት ያደርግልናል። 
እንዲሁም ያጽናናናል።
ልባችን ሲሰበር ወደ እኛ ይቀርባል።
አዎ፣ የይሖዋን ማሳሰቢያዎች እንሰማለን።
ችላ አንላቸውም።
ትኩረት ልንሰጣቸው እንፈልጋለን።
እንዲያውም መዝሙራዊው መዝሙር 119፡111 ላይ የተናገረውን እንመልከት።
እንዲህ ብሏል፦
“ማሳሰቢያዎችህ ልቤን ደስ ስለሚያሰኙ፣
ቋሚ ንብረቴ አደርጋቸዋለሁ።”
የይሖዋ ማሳሰቢያዎች ደስተኛ ያደርጉናል።
እንዲሁም አንድ ያደርጉናል።
በተጨማሪም ከእሱ ጋር እንድንሄድና
ተቀራርበን እንድንኖር ይረዱናል።
የይሖዋን ማሳሰቢያዎች አስመልክቶ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን አድርጓል።
ይሖዋ የሚነግረንን ስንሰማ ወደ እሱ ይበልጥ እቀርባለን።
ወንድሞቻችንን የማገልገል ፍላጎታችንም ያድጋል።
በአንድ የአገልግሎት ምድብ መካፈል
ምን እንደሚመስል ቀምሳችሁ ታውቃላችሁ?
አሁን ተመድባችሁ እያገለገላችሁ ቢሆንም
በሌላ ምድብ ማገልገል ምን እንደሚመስል ማየት ትፈልጋላችሁ?
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ምን እንደሚመስል የሚያስቃኝ
አዲስ ዓምድ መዘጋጀቱን ስንገልጽላችሁ ደስ ይለናል።
ርዕሱ ውሏቸው ምን ይመስላል? የሚል ነው።
በዚህ ዓምድ ላይ የሚቀርበው እያንዳንዱ ክፍል
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች በልዩ ልዩ የአገልግሎት ዘርፎች
የሚያሳልፉት የቀን ውሎ ምን እንደሚመስል ያሳየናል።
በዚህ ወር የሚቀርበው የመጀመሪያው ክፍል
ውሏቸው ምን ይመስላል?ተርጓሚዎች የሚል ነው።
ሰላም፣ እንዴት ናችሁ?
ሃናኪም እባላለሁ።
የምሠራው በኮርያ የምልክት ቋንቋ የትርጉም ክፍል ውስጥ ነው።
የትርጉም ክፍሉ መንፈሳዊ ምግቦችን
ከእንግሊዝኛ ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች ይተረጉማል።
ስንተረጉም ትክክለኛ የሆኑ፣ በቀላሉ የሚገቡና
የተለመዱ አገላለጾችን እንጠቀማለን።
በምልክት ቋንቋ ስንተረጉም
በጽሑፉ ላይ ያለውን ሐሳብ ወደ ቪዲዮ እንቀይረዋለን።
ይህን የምናደርገው የፊታችንን ገጽታ በመለዋወጥና እጆቻችንን በመጠቀም ነው።
አሁን ዛሬ የምንተረጉመውን ጽሑፍ እያነበብኩ ነው።
የሐሳቦቹ ቅደም ተከተል እንዴት እንደሆነ፣
ዋና ዋና ሐሳቦቹ የትኞቹ እንደሆኑና
በምልክት ቋንቋ ጥሩ አድርጌ መግለጽ የምችለው እንዴት እንደሆነ እያሰብኩ ነው።
ተርጓሚ ሆኖ ለማገልገል ጥሩ የቋንቋ ችሎታ ያስፈልጋል።
እኔ ወደ ምልክት ቋንቋ የትርጉም ሥራ ስገባ
የምልክት ቋንቋን በደንብ እንደምችለው ይሰማኝ ነበር።
ብዙ በተማርኩ ቁጥር ግን ብዙ የማላውቀው ነገር እንዳለ ተገነዘብኩ።
ስሠለጥን ለቋንቋው ባሕርይና አወቃቀር ትኩረት መስጠት ጀመርኩ።
መስማት የተሳናቸው ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው
የሚጠቀሙባቸውን ምልክቶች ማስተዋል ጀመርኩ።
ይህም ሐሳቡን በግልጽና በቀላሉ በሚገባ መንገድ ለማስተላለፍ ረድቶኛል።
አንድ የትርጉም ቡድን በአብዛኛው ሦስት አባላት አሉት።
እያንዳንዱ የቡድኑ አባል ትርጉሙ ትክክለኛና
በቀላሉ የሚገባ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት።
የምልክት ቋንቋን በጽሑፍ ማስፈር ስለማይቻል
የትርጉም ሥራችንን የምንሠራው ቪዲዮ እየቀረጽን ነው።
ዛሬ የምንተረጉመው ብሉ ዌል ስለተባለ ዓሣ ነባሪ ነው።
ግን ሦስታችንም ዓሣ ነባሪን የምንገልጸው በተለያየ መንገድ ነው።
ስለዚህ ‘ብዙ ቦታ የሚጠቀሙበት የትኛውን መጠሪያ ነው?’
የሚለውን እየተወያየን ነው።
አንዳንድ ጊዜ በትርጉም ሥራችን ላይ
ትክክለኛውን መግለጫ ማግኘት ይከብደናል።
በዚህ ጊዜ አንድ ላይ ሆነን በሰፊው እንወያይበታለን።
ከዚያም ሁላችንንም የሚያስማማ ጥሩ መግለጫ እናገኛለን።
በዚህ ጊዜ ይሖዋ እንደረዳን ይሰማናል።
ይህ ደስ የሚል ስሜት ነው የሚፈጥረው።
በትርጉም ቡድናችን ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች
በተለያየ ሕይወት ውስጥ ያለፉ ናቸው።
የምንሠራው አብረን ነው።
ጉባኤያችን አንድ ነው።
አብረንም እናገለግላለን።
በቃ ልክ እንደ ቤተሰብ ነን።
አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት
በቅርቡ የትርጉም ሥራው ሂደት ተቀይሯል።
አሁን የቀዳናቸውን ቪድዮዎች ኤዲት የምናደርገው
ማለትም ቦታ ቦታ የምናስይዘው እኛው ራሳችን ነን።
መጀመሪያ ላይ ሥራው ከባድ ስለመሰለኝ
‘እችለው ይሆን?’ ብዬ ተጨንቄ ነበር።
አሁን ግን ላገኘሁት ሥልጠና ምስጋና ይግባውና ብዙ ልምድ እየቀሰምኩ ነው።
እሺ፣ አሁን ጨርሰናል።
ከጓደኛዬ ከሂዮንጂ ጋር የምንሠራውም የምንኖረውም አንድ ላይ ነው።
ጉባኤያችንም አንድ ነው።
ከእሷ ጋር ሁሉንም ነገር ማውራት ስለምችል በጣም ደስተኛ ነኝ።
አንድን ጽሑፍ በምተረጉምበት ወቅት
በዋነኝነት ትኩረት የማደርገው መልዕክቱን
እንዴት ግልጽ በሆነ መንገድ ላስተላልፍ በሚለው ላይ ነው።
በኋላ ትምህርቱ ሲወጣ ግን
‘ይሖዋ ሊያስተምረኝ የፈለገው ምንድን ነው?
ተግባራዊ የማደርገው እንዴት ነው?’
የሚለውን እያሰብኩ አጠናዋለሁ።
ብዙ ጊዜ የተወያየንበትን አንድ ጽሑፍ እንኳ
ተተርጉሞ ከወጣ በኋላ ሳየው አዲስ ሐሳብ ሆኖ ነው የማገኘው።
ይህ ደግሞ መንፈሳዊ ጥቅም ለማግኘት ከፈለግኩ
በትምህርቱ ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መመደብና
ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብኝ አስገንዝቦኛል።
ወላጆቼ መስማት ስለማይችሉ የምልክት ቋንቋ የተማርኩት ገና በልጅነቴ ነው።
ትርጓሚ ሆኜ ስሠራ ደግሞ ወንድሞችና እህቶች
መስማት የማይችሉ ጥቂት ሰውን ለመርዳት
ምን ያህል እንደሚደክሙ ሳይ ልቤ በጥልቅ ተነካ።
ይሖዋ በሚያሳያቸው ፍቅርና እንክብካቤ በጣም ነው የተደነቅኩት።
መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ልብ የሚነካ
ለመረዳት ቀላል የሆነ ትርጉም ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጥረት አደርጋለሁ።
በምልክት ቋንቋ የሚጠቀሙ ወንድሞችና እህቶችን መርዳት መቻሌ
እርካታ አስገኝቶልኛል።
በተለይ ደግሞ የምልክት ቋንቋ ትርጉሙ
ወላጆቼን ስለጠቀማቸውና
ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡ ስለረዳቸው በጣም ደስተኛ ነኝ።
ተርጓሚ ሆኖ የማገልገልና
አምላክ በዛሬው ጊዜ እያከናወነው ያለውን ሥራ
በቅርበት የመመልከት አጋጣሚ በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።
ሌሎችም ወደዚህ ልዩ የአገልግሎት መብት እንዲገቡና
ይህን ስሜት እንዲያጣጥሙ ከልቤ እመኛለሁ።
እህት ኪም አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነጥብ አንስታለች።
ሥራዋ ከመንፈሳዊ ምግብ ጋር የተያያዘ ቢሆንም
ያንኑ መንፈሳዊ ምግብ ለመመገብና ለማጥናት
ጊዜ መመደብ እንዳለባት ተገንዝባለች።
ይህ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለምንካፈል ለሁላችንም ጥሩ ማሳሰቢያ ነው።
ወጣቶች ይህ ዓምድ
ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል እንደሚያነሳሳችሁ ተስፋ እናደርጋለን።
የሙዚቃ ቪዲዮአችንም የይሖዋ ቤተሰብ አባል መሆን የሚያስገኘውን ሌላ ጥቅም ያጎላል።
የምሥራቹን መልእክት ለአንድ ሰው ስናካፍልም ይሁን
በጉባኤ የሚገኝን አንድ አስፋፊ ስናበረታታ
በተገቢው ጊዜ ትክክለኛውን ነገር ለመናገር ጥረት እናደርጋለን።
ቃል ይሰብራል፣ ገድሎ ያሽራል፤
ቃል ጠብ ይጠራል፤ ቃል ያፋቅራል።
እሳት ’ሚበጀው ሲሆን በመላ፣
አንደበትም በጥበብ ሲገራ።
አቤት ጣ’ሙ፣ ደስ ማለቱ!
በጊዜው ሲሆን ቃል፣ ሲነገር በወቅቱ።
ጣፋጭ ለነፍስ፣ እንደ ማር እንጀራ፤
ፈውስ ነው ላጥንት፣ ’ሚጠግን ሰባራ።
ስጦታ ነው በ’ርግጥ፣ ለገባው ብልሃቱ።
በጊዜው ሲሆን ቃል፣ በወቅቱ።
ያሳያል ገልጦ የልብን ጓዳ፤
አንደበት አይናገር፣ ቀድሞ ካልተሰናዳ።
በጎ በጎውን ሲያስብ ልቦና፣
ያፈልቃል ውብ ቃል፣ የቃል ቀና።
አቤት ጣ’ሙ፣ ደስ ማለቱ!
በጊዜው ሲሆን ቃል፣ ሲነገር በወቅቱ።
ጣፋጭ ለነፍስ፣ እንደ ማር እንጀራ፤
ፈውስ ነው ላጥንት፣ ’ሚጠግን ሰባራ።
ስጦታ ነው በ’ርግጥ፣ ለገባው ብልሃቱ።
በጊዜው ሲሆን ቃል፣ በወቅቱ።
አቤት ጣ’ሙ፣ ደስ ማለቱ!
በጊዜው ሲሆን ቃል፣ ሲነገር በወቅቱ።
ጣፋጭ ለነፍስ፣ እንደ ማር እንጀራ፤
ፈውስ ነው ላጥንት፣ ’ሚጠግን ሰባራ።
ስጦታ ነው በ’ርግጥ፣ ለገባው ብልሃቱ።
በጊዜው ሲሆን ቃል፣ በወቅቱ።
አሁን ውድ ሀብት ለማግኘት እንቆፍር።
አጫጫር የትንቢት መጽሐፍት ከሚባሉት 12 መጽሐፍት መካከል
ዛሬ የናሆምን መጽሐፍ እናያለን።
ቪዲዮውን ስትመለከቱ ልትሠሩባቸው ወይም
ምርምር ልታደርጉባቸው የምትችሉ ነጥቦችን ፈልጉ።
ሳምንታዊ የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንን እንጀምር።
ከናሆም መጽሐፍ ብዙ መንፈሳዊ ዕንቁዎችን እናገኛለን።
ልክ ነህ!
ትኩረት የሚያደርገው በይሖዋ ሉዓላዊነትና በስሙ መቀደስ ላይ ነው።
አዎ!
ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን ሙሉ ጥቅም ለማግኘት
የማወቅ ጉጉት ኖሮን ረጋ ብለን እንድናነብ ታማኙ ባሪያ ያሳስበናል።
ደስ የሚል ነጥብ ነው።
ስንፈጥን ብዙ ነገር ያመልጠናል።
ትክክል ነው!
መጽሐፉ ሲጀምር “በነነዌ ላይ የተላለፈ ፍርድ” ይላል።
ልክ ነህ።
ነነዌ!
ስለ ነነዌ የምናውቃቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ አይደል?
አዎ።
ነብዩ ዮናስ ወደዚያ ሲላክ ምን እንደተሰማው እናውቃለን።
አሦራውያን በጣም አስፈሪ ሰዎች ስለነበሩ ዮናስ ሸሽቷል።
ልክ ነው።
ናሆም ይሖዋ ይህንን መልዕክት እንዲያደርስ ሲልከው
ምን ነገሮች ወደ አእምሮው መጥተው ይሆን?
በጣም ተጨንቆ የነበረ ይመስለኛል።
የምርምር መርጃ መሣሪያ ላይ ነነዌ ይህን ያውቁ ኖሯል?
ነነዌ የደም ከተማ የተባለችው ለምን ነበር?
በሚለው ሥር የምናገኘው መረጃ ይህን ይጠቁማል።
ጥሩ ዘዴ ነው።
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የምርምር መርጃውን መጠቀም።
እዚያ ላይ የተጠቀሰው አንዱ ጽሑፍ
አንድ ምሁር ያሉትን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦
'’ወንዶችና ሴቶች ልጆች ከነሕይወታቸው በእሳት ይቃጠሉ፣
ወንዶች በስቅላት ይቀጡ፣ በቁማቸው ቆዳቸው ይገፈፍ፣
ዓይናቸው ይጠፋ ወይም እጃቸው፣ እግራቸው፣
ጆሯቸውና አፍንጫቸው ይቆረጥ ነበር።”
ሲዘገንን!
ናሆም መጨነቅ ሲያንሰው ነው።
ግን እንዲህ የተሰማው እሱ ብቻ አይመስለኝም።
ይህን የፍርድ መልዕክት የተናገረው
በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን ሳይሆን አይቀርም።
ኢዮስያስ የሐሰት አምልኮን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።
ስለዚህ ንጉሥ ኢዮስያስም ሆነ እስራኤላውያን
ይሖዋን ለማምለክ ጥረት ሲያደርጉ ተጨንቀው፣ ፈርተው ይሆን?
ደግሞም በወቅቱ ኃያል መንግሥት የነበሩት አሦራውያን
የፈለጉትን ማድረግ ይችሉ ነበር።
ምናልባትም እስራኤላውያን የሐሰት አምልኮን ለማስወገድ የሚያደርጉት ጥረት
አሦራውያንን ሊያስቆጣ ይችላል ብለው ፈርተው
ወይም ‘በሰማርያ ላይ ያደረጉትን በእኛም ላይ ይደግሙት ይሆን?’
ብለው ሰግተው ይሆናል።
የኖርነው በዚያ ወቅት ቢሆን ስለልጆቻችን በጣም እንጨነቅ ነበር።
ልክ ነሽ!
ግን ይሖዋ ቁጥር 3 ላይ ሉዓላዊነቱን ስለሚጠቀምበት መንገድ ሲናገር
ኃይሉ ታላቅ ቢሆንም ለቁጣ የዘገየ እንደሆነ አስታውሷቸዋል።
ምርምር ሳደርግ እንደተገነዘብኩት ይሖዋ ለቁጣ የዘገየ መሆኑን
በቀጥታ ከታላቅ ኃይሉ ጋር አያይዞ ከጠቀሰባቸው
ጥቂት ቦታዎች መካከል አንዱ ይህ ነው።
የሕዝቡ ትኩረት በእሱና ባለው ኃይል ላይ እንዲያርፍ እንጂ
በአሦራውያን ላይ እንዳይሆን ፈልጓል።
በጣም የሚያጽናና ነው።
ይሖዋ በመቀጠል ቁጥር 15 ላይ እንዲህ ብሏል፦
“ይሁዳ ሆይ፣ በዓሎችሽን አክብሪ፤ ስእለትሽን ፈጽሚ፤
“ከእንግዲህ ወዲህ የማይረባ ሰው በመካከልሽ አያልፍምና።
እንዲህ ያለው ሰው ሙሉ በሙሉ ይወገዳል።”
‘ስለዚህ አሦራውያንን እስካጠፋቸው እኔን ያለስጋት ማምለካችሁን ቀጥሉ።
በዓሎቻችሁን አክብሩ’ እያላቸው ነበር።
‘ተማመኑብኝ’ እያለ ነው።
የሚገርመው ከጊዜ በኋላ ታላቅ ኃይሉን በመጠቀም ሙሉ በሙሉ ስላጠፋት
አንዳንድ ተቺዎች “ነነዌ የምትባል ከተማ ቀድሞውኑም አልነበረችም” እስከማለት ደርሰዋል።
ኢዮስያስ፣ ናሆም እንዲሁም የይሖዋ ሕዝቦች በአጠቃላይ
ትልቅ እፎይታ አግኝተው መሆን አለበት።
ይሖዋን በሰላምና በደስታ ማምለክ ችለዋል።
በይሖዋ ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ከጭንቀት ገላግሏቸዋል።
በጣም ግሩም ነጥብ ነው ያነሳሽው።
ቆይ ማስታወሻዬ ላይ ልጻፈው።
ይሖዋ የሚገዛበት መንገድ እንድንተማመንበት ያደርገናል።
ልክ ነህ!
ከይሖዋ ጋር ባለን ወዳጅነት ረገድ የሚጠቅም ትምህርት ይዟል።
ትክክል ነሽ፣ ይሖዋ የሚገዛበት መንገድ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ያሳየናል።
ጥቅሱ በጣም አስገርሞኛል።
“ይሖዋ ለቁጣ የዘገየ ነው፤ ኃይሉም ታላቅ ነው” ይላል።
ግን አብዛኞቹ ሰዎች ኃይል ሲኖራቸው እንደዚህ አይደሉም።
ይሖዋ እንደ አሦራውያን ላሉ ጨካኝና ዓመፀኛ ጠላቶቹ እንኳ
ለቁጣ የዘገየ ከሆነ እኔንም በትዕግሥት ይይዘኛል።
ስህተት ስሠራ የሚቀናኝ “በቃ ይሖዋ በእኔ ተስፋ ቆርጧል” ብሎ ማሰብ ነው።
በዚህ ዘገባ ላይ ማሰላሰሌ ግን
ይሖዋን ልክ እንደ ታጋሽና እንደ አፍቃሪ አባት እንዳየው አድርጎኛል።
ይሖዋ ከእኔም ጋር በተያያዘ ለቁጣ የዘገየ መሆኑ የፍቅሩ መገለጫ ነው።
ይህም ወዳጄ እንደሆነ እርግጠኛ እንድሆን ያደርገኛል።
እውነትህን እኮ ነው!
አንዳንዴ በራሳችን ላይ ጨካኝ ጠላቶች እንሆናለን።
ውስጣችን ያለማቋረጥ ቢኮንነንም ይሖዋ ግን እንደዛ አይደለም።
ስለዚህ ይሖዋ ከእኔ ጋር በተያያዘ ለቁጣ የዘገየ ከሆነ
እኔም ለራሴ እንደዛ መሆን አለብኝ።
አንዳንዴ ራሴን ይሖዋ በሚያየኝ መንገድ ለማየት
ራሴን ማስገደድ ያስፈልገኛል።
ይህ በጉባኤ ወይም በቤተሰብ ውስጥ የተወሰነ ሥልጣን ላለንም
ጠቃሚ ትምህርት ይዟል።
ራሴን እንዲህ ብዬ እንድጠይቅ አነሳስቶኛል፦
‘ለቁጣ የዘገየሁ ነኝ?’
‘ቶሎ በቁጣ የምገነፍል ከሆነ ማንን እየመሰልኩ ነው?’
‘ይሖዋስ ምን ይሰማዋል?’
ግሩም ነጥብ ነው!
ይሖዋ ስላለው ኃይልም ሳስብ ነበር።
አሦራውያን ከይሖዋ አንጻር ኢምንት ነበሩ።
ስለዚህ እስራኤላውያን የሚፈሩበት ምንም ምክንያት አልነበረም።
ዛሬም የምንኖረው በሰይጣን ዓለም ውስጥ ቢሆንም መፍራት የለብንም።
ይሖዋ ስለሚረዳኝ ችግሮች ሲያጋጥሙኝ
ትኩረቴን ይሖዋ ኃይሉን በሚጠቀምበት መንገድ ላይ ማድረግ አለብኝ።
እንደዛ ከሆነ አልፈራም።
ችግሩን ከራሴ ሳይሆን ይሖዋ ካለው ኃይል አንጻር በማየት
ልበ ሙሉ መሆን እችላለሁ።
ልክ ብለሻል!
ድረ ገጻችን ላይ የሚወጡ ተሞክሮዎችን ማንበቤም ጠቅሞኛል።
ስደትን እየተቋቋሙ ያሉ ወንድሞችና እህቶችን ተሞክሮዎች ማንበቤ
እኔም ስደትን ለመቋቋም ጥረት ሳደርግ
ይሖዋ እንድጸና እንደሚረዳኝ እንድተማመንበት አድርጎኛል።
የእነሱ ጽናት ይሖዋ ዛሬም ቢሆን ሕዝቡን ለመርዳት
ኃይሉን እየተጠቀመ እንደሆነ ያሳያል።
እውነትም ይሖዋ ለቁጣ የዘገየ ነው።
ኃይሉም ታላቅ ነው።
ልክ ነህ!
እሺ፣ እስቲ ዋና ዋና ነጥቦቹን መለስ ብዬ ልከልስ።
የማወቅ ጉጉት ኖሮን ረጋ ብለን ማንበብ፣
የምርምር መርጃውን በጥሩ ሁኔታ መጠቀምና
አገዛዙ ስለ እሱ ምን እንደሚያስተምረን ማስተዋል።
ልክ ነሽ!
ከዘገባው ሌሎች ትምህርቶችም እናገኛለን።
ለምሳሌ ስለ ነነዌ ጥፋት ናሆም የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ማግኘቱ
እምነታችንን የሚያጠናክርልን እንዴት ነው?
ጥናታችንን እንቀጥል።
ሌላው ያስተዋልኩት ነጥብ ደግሞ . . .
በዚህ ፕሮግራም ላይ ይሖዋ አምላክ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ካሉት ሁሉ
እጅግ አፍቃሪው አባት እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ተመልክተናል።
የእሱ ቤተሰብ አባል ለመሆን የምናደርገው ማንኛውም ጥረት አያስቆጭም።
ክርስቲያናዊ ባሕርይ የሆነውን ፍቅርን በማዳበር
ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ፍጹም በሆነ አንድነት እንተሳሰራለን።
ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ማጠናከራችን
ድርጅቱንና የመንግሥቱን ሥራ እንድንደግፍ የተሰጠንን ተልእኮ
በአግባቡ እንድንወጣ ያስችለናል።
ያላሰብናቸው ችግሮች ሲያጋጥሙን ይሖዋ አባታችንና
የማይናወጥ ዓለታችን እንደሆነ ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም።
በዚህ ወር ሰላምታ ይዘንላችሁ የመጣነው
በመካከለኛው አፍሪካ፣ ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ ላይ ከምትገኘው ከጋቦን ነው።
የአፍሪካ ኤደን በመባልም ትታወቃለች።
85 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ክፍል በደን የተሸፈነ ሲሆን
የኮንጎ ፏፏቴዎች የሚገኙትም በዚያ ነው።
በሉዋንጎ ብሔራዊ ፓርክ ዝሆኖች በባሕሩ ዳርቻ ሲንቀሳቀሱ ልታዩ ትችላላችሁ።
ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረቡ እነዚህ የጫካ ዝሆኖች
በዓለም ላይ በብዛት የሚገኙት በጋቦን ነው።
በጋቦን ጎሬላዎች፣ ማንድሪልስ የተባሉ ባለ ቀለም ዝንጀሮዎችና
ቺምፓንዚዎች ይገኛሉ።
በጋቦን አቅራቢያ በሚገኘው ውቅያኖስም
ብዙ የዓሣ ዝርያዎችና እንስሳት አሉ።
ወደ 20 የሚጠጉ የዶልፊንና የዓሣነባሪ ዝርያዎች ይገኛሉ።
እነዚህን ግዙፍ የሆኑ የባሕር እንስሳት በቅርበት ለማየት
ብዙዎች ጋቦንን ይመርጣሉ።
ሆኖም ወደ ጋቦን እፉኝት መቅረብ የለባችሁም።
መርዛማ ከሆኑ እባቦች መካከል
ረጅም ጥርስ ያላቸው እነዚህ ናቸው።
የጥርሳቸው ርዝማኔ እስከ 5 ሴንቲ ሜትር ይደርሳል።
ደግነቱ የተረጋጉና ብዙውን ጊዜ ሰዎችን የማይተናኮሉ መሆናቸው ነው።
ዋና ከተማ ሊብራቪል የተቆረቆረችው ነፃ በወጡ ባሮች በ1849 ነው።
ከተማዋ ውብ በሆኑ ሕንፃዎች፣ መናፈሻዎችና የባሕር ዳርቻዎች ትታወቃለች።
በደቡብ ምሥራቅ የሚገኘውን ፍራንስ ቪል ከተማ አልፎ
እንደ ፑቫራ ፏፏቴ ያሉ ድንቅ የተፈጥሮ መስህቦች ይገኛሉ።
በ1957 ሁለት ወንድሞች ሥራ ለመፈለግ
ከኮንጎ ብራዛቪል ወደ ደቡብ ጋቦን መጡ።
በዛም አንቶኒ ሞራንጋ ለሚባል ሰው መሠከሩ።
እሱም ፈጣን እድገት አድርጎ ሰኔ 1957 ተጠመቀ።
በጋቦንም የመጀመሪያው የይሖዋ ምሥክር ለመሆን በቃ።
በዚያው ወቅት በአንድ የግንባታ ድርጅት ውስጥ ይሠሩ የነበሩ
ከኮንጎ የመጡ ይሖዋ ምሥክሮች ወደ ጋቦን ተዛወሩ።
ከወንድም ሉባንጋ ጋር ሆነው መስበክ የጀመሩ ሲሆን
በተከራዩት አነስተኛ ቤት ውስጥ መሰብሰብ ጀመሩ።
ቅዳሜ ቅዳሜ ከሰዓት ላይ
አግዳሚ ወንበሮችን ውጪ ደርድረው ሕዝብ ንግግር ይሰጡ ነበር።
በዚህም ምክንያት የአግዳሚ ወንበሮቹ ሃይማኖት’ የሚል ቅጽል ስም ተሰጣቸው።
በ1964 የመንግሥቱ ሥራ ሕጋዊ እውቅና አገኘ።
ከዚያም ሚስዮናውያን ወደ አገሪቱ ተመደቡ።
ምሥራቹን ለብዙዎች ለማድረስ እሁድ እሁድ
የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን በራዲዮ ያስተላልፉ ነበር።
ሚያዝያ 1970 መንግሥት በድንገት በስብከቱ ሥራ ላይ እገዳ ጣለ።
ሚስዮናውያንንም አባረረ።
ስብሰባዎችንም ከለከለ።
በእገዳ ወቅት ወንድሞችና እህቶች የተለየ ቅንዓት ነበራቸው።
ምሽት ላይ የጉባኤውም ሆነ ትላልቅ ስብሰባዎችን ያካሄዱ ነበር።
ከጊዜ በኋላ ግን ሁኔታዎች ተሻሻሉ።
የስብሰባ አዳራሾችን መገንባት ቻሉ።
ትላልቅ ስብሰባዎችን ማድረግ ጀመሩ።
እንደገና በራዲዮ ፕሮግራሞችን ማሰራጨት ጀመሩ።
ፕሮግራሙ በጣም ተወዳጅ ከመሆኑ የተነሳ
በ2004 የአገሪቱ ብሔራዊ ጋዜጣ ስለ ሁኔታው ጽፎ ነበር።
የሬዲዮ ፕሮግራሙን ከሚያቀርቡት ወንድሞች መካከል አንዱ እንደተናገረው
አንዳንዶች በድምፅ ስላወቁት ብቻ
ከእሱ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊጀምሩ ችለዋል።
በዛሬ ጊዜ ከ4,600 በላይ የሚሆኑ አስፋፊዎች
የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበኩ ነው።
ከ8,000 በላይ የሚያክሉ ጥናቶችን በተለያዩ ቋንቋዎች ይመራሉ።
ለምሳሌ በፈረንሳይኛ፣ በፎንግ፣ በሜጌኔ፣ በፑኑ፣
በዛቢና በቴኬ ቋንቋዎች ጥናቶችን ይመራሉ።
በቅርቡ ደግሞ 28 የሚሆኑ ወጣት ወንድሞችና እህቶች
ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተካፍለዋል።
ትምህርቱ የተሰጠው በኦካላ ሊብራቪል በሚገኝ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ነው።
116 አስፋፊዎች ያሉት የኦካላ ጉባኤ
በቅርብ ጊዜ ከ140 በላይ የሆነ
ከፍተኛ የጥናቶች ቁጥር ሪፖርት አድርጓል።
በተጨማሪም 287 ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተዋል።
በኦካላ ጉባኤ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች
ሞቅ ያለ ፍቅራዊ ሰላምታቸውን ልከውላችኋል።
ይህ ከይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚተላለፍላችሁ
JW ብሮድካስቲንግ ነው።