JW subtitle extractor

JW ብሮድካስቲንግ—ኅዳር 2026

Video Other languages Share text Share link Show times

ለJW ብሮድካስቲንግ ፕሮግራማችን እንኳን ደህና መጣችሁ!
በዚህ ወር ፕሮግራማችን አመለካከታችንን ለማስተካከል ፈቃደኛ መሆናችን እንዴት እንደሚጠቅመን እናያለን።
ልባቸውንም ሆነ ቤታቸውን ክፍት በማድረጋቸው የተባረኩ ሁለት ቤተሰቦችን እንተዋወቃለን።
ይሖዋ እያንዳንዳችንንም ሆነ ድርጅቱን የሚያጠራው እንዴት እንደሆነ በጥልቀት በመርመር
ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመለከታለን።
በተጨማሪም ቤተሰባችንን ስንንከባከብ ለይሖዋ አገልግሎት ቅድሚያ መስጠታችን
የተትረፈረፈ በረከት የሚያስገኝልን እንዴት እንደሆነ እናያለን።
ይህ JW ብሮድካስቲንግ ነው።
የንግግራችን ጭብጥ “የማስታወስ ችሎታችሁን በጥበብ ተጠቀሙበት” የሚል ነው።
‘ይህ እንዴት ይሆናል?’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል።
‘የማስታውሰውን መምረጥ አልችልም።’
አዎ፣ በተወሰነ መጠን ይህ እውነት ነው።
ግን በአእምሯችን ውስጥ የምናውጠነጥነውን ነገር መምረጥ እንችላለን።
የምናስታውሰው ያንን ነው።
በዚህ ንግግር ላይ የማስታወስ ችሎታችንን በመጠቀም ረገድ ከይሖዋ የምንማረውን እናያለን።
ከዚያም የማስታወስ ችሎታችን ሌሎችን ከመውደድና ከማገልገል ጋር እንዴት እንደሚያያዝ እናያለን።
ይሖዋ ከእኛ ጋር በተያያዘ ለማስታወስ የሚመርጠው ምንድን ነው?
እባካችሁ ዕብራውያን 6:10ን አብረን እናንብብ።
እንዲህ ይላል፦
“አምላክ ቅዱሳንን በማገልገልም ሆነ ወደፊትም ማገልገላችሁን በመቀጠል
የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።”
ይሖዋ የሚያስታውሰውን ልብ አላችሁት?
ያደረግናቸውን መልካም ነገሮች ያስታውሳል።
ለዚህ ጥቅስ የተዘጋጀው የጥናት ማስታወሻ እንዲህ ይላል፦
“አንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ያደረገውን መልካም ነገር መርሳት በአምላክ ዓይን ፍትሕ እንደማዛባት ይቆጠራል።”
ይህ አገላለጽ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ምን ያህል እንደሚያስብ የሚያሳይ አይደለም?
እርግጥ ይሖዋ የፈጸምናቸውን ኃጢአቶችና የሠራናቸውን ስህተቶች ጨምሮ ስለ እኛ እያንዳንዷን ነገር ያውቃል።
ግን ለማስታወስ የሚመርጠው እንዲህ ያሉ አሉታዊ ነገሮችን አይደለም።
ለምሳሌ፣ ትውስታችንን ከቤተ መጻሕፍት ጋር ልናመሳስለው እንችላለን።
ይሖዋ በእያንዳንዱ መደርደሪያ ላይ ያስቀመጥነውን እያንዳንዱን መጽሐፍ ያውቃል።
አንዳንዶቹ የሠራናቸውን ስህተቶችና ኃጢአቶች የያዙ ናቸው።
ሌሎቹ ደግሞ ያደረግናቸውን ጥሩ ነገሮች የያዙ ናቸው።
ይሖዋ መጥፎዎቹ መጻሕፍት የት እንዳሉ ጠንቅቆ ያውቃል።
ያም ቢሆን ትኩረት ለማድረግ የሚመርጠው በየትኞቹ መጻሕፍት ላይ ነው?
መልካም ሥራችንን በያዙት ላይ!
ይሖዋ የማስታወስ ችሎታውን ከተጠቀመበት መንገድ የምንማረው ምንድን ነው?
ወደ ዕብራውያን 6:10 ተመልሰን እዚያ ላይ የተጠቀሱትን ሁለት ነገሮች እንመልከት።
የመጀመሪያው ለይሖዋ ስም የምናሳየው ፍቅር ነው።
የይሖዋን ስም የመሸከም መብት በማግኘታችን እንኮራለን።
ይህ ደግሞ የይሖዋን ስም የሚያስነቀፍ ነገር አለማድረግን ይጨምራል።
አነጋገራችን፣ አለባበሳችን፣ ድርጊታችን የይሖዋ ስም እንዲከበር ሊያደርግ ይችላል።
ወይም በተቃራኒው!
1 ቆሮንቶስ 10:31 የምታደርጉትን ማንኛውንም ነገር
“ለአምላክ ክብር አድርጉ” የሚል ማሳሰቢያ የሚሰጠን ለዚህ ነው።
ሁሉም ሰው የይሖዋ ስም ቅዱስ እንደሆነና ትልቅ ቦታ እንደምንሰጠው እንዲያውቅልን እንፈልጋለን።
ሰዎች ስሙን እንዲያውቁ በማድረግም ለይሖዋ ስም ያለንን ፍቅር ማሳየት እንችላለን።
ይህ ደግሞ ምሥራቹን መስበክንም ይጨምራል።
ስለዚህ የአገልግሎታችንን ጥራት ለማሻሻል ጥረት ማድረግ አለብን።
ሳንረሳ ለአገልግሎት አስቀድመን መዘጋጀት ይኖርብናል።
ከሰዎች ጋር ውይይት መጀመራችን ጥሩ ነው።
በዚህ ብቻ ግን አናበቃም።
የሆነ የሚጠቅማቸው ነገር ለማካፈል እንጥራለን።
መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከርንም አንረሳም።
ምንም ዓይነት አጋጣሚዎች እንዲያመልጡንም አንፈልግም።
ለራሳችን ግብ ማውጣትንም አንዘነጋም።
ሁኔታችን የሚፈቅድ ከሆነ ደግሞ በየሳምንቱ በአገልግሎት ለመካፈል ፕሮግራም እናወጣለን።
ይህንንም መዘንጋት አይኖርብንም።
ግባችን ለምሥራቹ ስንል ሁሉን ነገር ማድረግና ለይሖዋና ለስሙ ያለንን ፍቅር ማሳየት ነው።
ይህንን እናስታውስ።
ዕብራውያን 6:10 ላይ የተጠቀሰው ልናተኩርበት የምንፈልገው ሁለተኛው ነጥብ ቅዱሳንን ማገልገላችሁን ቀጥሉ የሚለው ነው።
ማገልገላችሁን ቀጥሉ!
እዚህ ላይ “ቅዱሳን” የሚለው የሚያመለክተው በመንፈስ የተቀቡ የክርስቶስ ተከታዮችን ነው።
ያኔ የነበሩ ዕብራውያን ክርስቲያኖች በመንፈስ የተቀቡ ወንድሞቻቸውን በተለያየ መንገድ አገልግለዋል።
የተቸገሩትን ለመርዳት የቁሳቁስ ወይም የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።
ጳውሎስ ከዚህ በፊት ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለመርዳት ያደረጉትን በመጥቀስ አመስግኗቸዋል።
ይህ ብቻ ግን አይደለም።
ወደፊት ስለሚያደርጉትም ነገር አመስግኗቸዋል።
ዕብራውያን 6:10 ላይ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖች በሙሉ ይሠራል።
ለሌሎች መልካም ነገር ማድረጋችሁን አትርሱ።
እኛም አንድ ሰው ደግነት ወይም ልግስና ሲያሳየን እንደሰታለን።
በፍቅር ተነሳስተን ለሌሎች ስንሰጥ ግን ከዚህ የበለጠ እንደሰታለን።
ሌሎችን ለመርዳት ልናደርጋቸው የምንችላቸውን ነገሮች ዘርዝረን ልንጨርሳቸው አንችልም።
ብዙ ናቸው።
ለምሳሌ በተፈጥሮ አደጋ ለተጠቁ፣ ከባድ ሕመም ላጋጠማቸው
ወይም በእምነታቸው ምክንያት ስደት ለደረሰባቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ማቅረብ እንችላለን።
ሌሎችን መርዳት የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ በጉባኤያችን ውስጥ የሚገኙትን ማበረታታትና ማመስገን ነው።
ለወንድሞቻችን መልካም የምናደርግበት ዋናኛው መንገድ ስለ እነሱ መጸለይ ነው።
ነጥቡ ምንድን ነው?
ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ሁላችንም ምሳሌ 3:27 ላይ ያለውን ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ እንፈልጋለን።
“ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችል አቅም ካለህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አትበል።”
የአምላክን ስም መውደዳችንና ለሌሎች መልካም ማድረጋችንን ካልረሳን፣
የማስታወስ ችሎታችንን በጥበብ እየተጠቀምንበት ነው ሊባል ይችላል።
ከማስታወስ ችሎታችን ጋር በተያያዘ የሚያጋጥመን አንዱ ፈታኝ ሁኔታ መርሳት የምንፈልጋቸውን ነገሮች ማስታወሳችን ነው።
በተለይ አንድ ሰው ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርግብን ያን መርሳት ከባድ ነው።
ድርጊቱን ማሰብ ወይም ሰውየውን ማስታወሳችን ብቻ እንኳ ያ ስሜት እንዲያገረሽብን ሊያደርግ ይችላል።
ፈጽሞ ሊለወጥ እንደማይችል፣ ይቅርን ልንለው እንደማንችል ሊሰማን ይችላል።
እስቲ ሁለት ተቃራኒ ምሳሌዎችን እንመልከት።
ስለ ንጉሥ ዳዊትና ስለ ሺምአይ በሚናገረው ዘገባ እንጀምር።
ሺምአይ የንጉሥ ሳኦል ዘመድ ነው።
በንጉሥ ዳዊት ላይ ለብዙ ዓመታት ቂም ይዞ ቆይቷል።
ምክንያቱም ከሳኦል ቤት ንግሥናው እንዲወሰድ ያደረገው ዳዊት እንደሆነ ተሰምቶታል።
2 ሳሙኤል 16 እንደሚነግረን ሺምአይ ዳዊትና ሰዎቹን እየተራገመ ድንጋይ ይወረውርባቸውና አቧራ ይበትንባቸው ነበር።
ይህ ሺምአይ ለዳዊት ከፍተኛ ንቀት እንዳለው የሚያሳይ ድርጊት ነበር።
እንዲያውም ከዳዊት ሰዎች አንዱ የሆነው አቢሳ ሺምአይን ለመግደል ፈልጎ ነበር።
ዳዊት ግን ከለከለው።
ዳዊት በትሕትና የበቀል ስሜቱን ገትቶ ጉዳዩን በይሖዋ እጅ ተወው።
ዳዊት በዚህ ጊዜ አስደናቂ የሆነ ራስን የመቆጣጠር ችሎታ እንዳለው አሳይቷል።
በኋላ ዳዊት ወደ ንግሥናው ተመለሰ።
ሺምአይም ንስሐ ገብቶ ይቅርታ ጠየቀ።
ግን አሁንም አቢሳ ካልገደልኩት አለ።
ዳዊት ደግሞ አሁንም “አይሆንም” ብሎ ከለከለው።
ሌላው ቀርቶ ዳዊት ሺምአይን እንደማይገድለው ማለለት።
ከዚህ በግልጽ ማየት እንደምንችለው ዳዊት ይህን ጉዳይ የያዘው ይሖዋን በእጅጉ በሚያስደስት መንገድ ነው።
ግን ዳዊት ከመሞቱ በፊት ለልጁ ለሰለሞን ምን እንዳለው አንደኛ ነገሥት 2:8, 9 ላይ እናብብ።
1 ነገሥት 2:8, 9 እንዲህ ይላል፦
“በተጨማሪም ከባሁሪም የመጣው ቢንያማዊው የጌራ ልጅ ሺምአይ አብሮህ አለ።
“ወደ ማሃናይም በሄድኩበት ዕለት ከባድ እርግማን የረገመኝ እሱ ነው፤
“ሆኖም እኔን ለማግኘት ወደ ዮርዳኖስ በወረደ ጊዜ ‘በሰይፍ አልገድልህም’ ብዬ በይሖዋ ማልኩለት።
“አንተ ጥበበኛ ስለሆንክና በእሱ ላይ ምን ማድረግ እንዳለብህ ስለምታውቅ ሳትቀጣ አትተወው፤
ሽበቱ በደም ወደ መቃብር እንዲወርድ አድርግ።”
ዳዊት ባሁሪም ላይ ሺምአይን ሲያገኘው ዕድሜው 60ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም።
የሞተው ደግሞ በ70 ዓመቱ ነው።
ስለዚህ ዳዊት ለበርካታ ዓመታት ጉዳዩን አልረሳውም ማለት ነው።
ሺምአይን እያሰበ ሲብሰለሰል ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ዳዊት ይህን ያደረገው ለምን እንደሆነ አይነግረንም።
ግን ይህ ታሪክ አንድ ነገር ግልጽ ያደርግልናል።
አንድ ሰው ደግነት የጎደለው ነገር ሲያደርግብን ወይም ሲበድለን
ጉዳዩን መተው ከባድ ሊሆንብን ይችላል።
በዚህ ወቅት ጉዳዩን በጥሩ መንገድ ብንፈታውም እንኳ የስሜት ቁስሉ ለዓመታት በውስጣችን ሊቆይ ይችላል።
ታዲያ ጉዳዩን ለመተውና ይቅር ለማለት ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው?
ኢየሱስ ከጴጥሮስ ጋር በተያዘ የተወውን ምሳሌን እንመልከት።
ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት ጴጥሮስ ፈጽሞ እንደማይክደው በተደጋጋሚ ተናግሮ ነበር።
ግን ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ኢየሱስን ፈጽሞ እንደማያውቀው ከአንዴም ሦስቴ በመናገር ወዳጁን ካደው።
እስቲ አስቡት፦
ኢየሱስ በምድር ላይ ካሳለፋቸው ጊዜያት ሁሉ ከባዱ ይህ ነው።
ወዳጆቹ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ከጎኑ ሊሆኑ ይገባ ነበር።
ሆኖም ምን አደረጉ?
የቅርብ ጓደኛውን ጴጥሮስን ጨምሮ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ።
ጴጥሮስ ያደረገውን ነገር ሲገነዘብ በጸጸት ስሜት ተወጦ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።
ታዲያ ኢየሱስ ምን አደረገ?
1 ቆሮንቶስ 15:5 እንደሚለው ከሞት ከተነሳ በኋላ ለጴጥሮስ ተገለጠለት።
ታዲያ ኢየሱስ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ጴጥሮስን ገሰጸው?
ወይም ደግሞ ምን ያህል እንዳዘነበት ተናገረ?
ማርቆስ 16:7 ላይ አንድ ፍንጭ እናገኛለን።
ጥቅሱን እናውጣው።
መልአኩ ወደ ኢየሱስ መቃብር ለመጡት ሴቶች ምን እንዳላቸው ተመልከቱ።
“ይልቁንስ ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ ‘ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል።
እንደነገራችሁም እዚያ ታዩታላችሁ’ በሏቸው።”
ለዚህ ጥቅስ የተዘጋጀው የጥናት ማስታወሻ እንዲህ ይላል፦
“ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በቡድን ከመገለጡ ጥቂት ቀደም ብሎ ለጴጥሮስ ለብቻው ሳይገለጥለት አልቀረም።
“ኢየሱስ በግለሰብ ደረጃ የሰጠው ይህ ትኩረትና መልአኩ ለሴቶቹ በነገረው መልክት ላይ ጴጥሮስ በስም መጠቀሱ
“የቅርብ ወዳጁ የሆነውን ኢየሱስን ‘አላውቀውም’ ብሎ ከአንዴም ሦስቴ ቢክደው
ይቅርታ እንደተደረገለት እርግጠኛ እንዲሆን ሳይያደርገው አይቀርም።”
ጴጥሮስ ይህንን ሲያውቅ ምን ያህል እፎይታ እንደተሰማው መገመት እንችላለን።
እርግጥ ነው ኢየሱስ ጴጥሮስ ያደረገውን ማስታወስ አይችልም ማለት አይደለም።
ሆኖም ኢየሱስ ለማስታወስ የመረጠው የጴጥሮስን ስተት ሳይሆን ጴጥሮስ ያሉትን መልካም ባሕርያት ነው።
ኢየሱስ ጴጥሮስን ይቅር በማለት ብቻ አልተወሰነም።
ወንድሞቹን የማበረታታት መብትም ሰጥቶታል።
ኢየሱስ የተወልን እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!
እኛም አንድ የቅርብ ወዳጃችን ከበደለን የማስታወስ ችሎታችንን በጥበብ በመጠቀም ኢየሱስን መምሰል እንችላለን።
አንድ ሌላ ምሳሌ እንጨምር።
የማስታወስ ችሎታችንን በጥበብ ስለመጠቀም።
አሁንም የዳዊትን ምሳሌ ነው የምንመለከተው።
ዳዊት ይሖዋ እሱን ለመርዳትና ለማዳን ያደረጋቸውን ነገሮች ያስታውስ ነበር።
እነዚህን ነገሮች ማስታውሱ የከፉ ነገሮች ሲያጋጥሙትም በይሖዋ እንዲተማመን ረድቶታል።
እስቲ መዝሙር 27:2, 3 ላይ ዳዊት ምን እንዳለ እንመልከት፦
“ክፉዎች ሥጋዬን ለመብላት ባጠቁኝ ጊዜ፣ ተሰናክለው የወደቁት ባላጋራዎቼና ጠላቶቼ ናቸው።
“ሠራዊት በዙሪያዬ ቢሰፍርም፣ ልቤ በፍርሃት አይዋጥም።
ጦርነት ቢከፈትብኝም እንኳ በልበ ሙሉነት እመላለሳለሁ።”
አቋሙን ልብ አላችሁ?
“ልቤ በፍርሃት አይዋጥም።”
“በልበ ሙሉነት እመላለሳለሁ።”
እኛስ ልክ እንደ ዳዊት ልበ ሙሉ መሆን እንችላለን?
አዎ፣ የማስታወስ ችሎታችንን በጥበብ ከተጠቀምን።
ለምሳሌ፣ ይሖዋ እናንተን የረዳበት ጊዜ ትዝ ይላችኋል?
ምናልባት አንድ አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሟችሁ፣
ጸሎታችሁን ሰምቶ ችግራችሁን ለመወጣት የሚያስችል ጥበብና ጥንካሬ ሰጥቷችሁ ይሆናል።
ይህን አስታውሱ።
ወይም ደግሞ አገልግሎታችሁን ለማስፋት ፈልጋችሁ፣ እዚህ ግባችሁ ላይ ለመድረስ እንቅፋት አጋጥሟችሁ ይሆናል።
ታዲያ ይሖዋ ከፊታችሁ የነበረውን ጋሬጣ እንዴት እንዳስወገደላችሁ ትዝ ይላችኋል?
ይህንንም አስታውሱ።
ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ ያጋጠሙን በርካታ ነገሮች አሉ።
ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ያሳለፍነውን ጊዜ ስናስብ፣ ቶሎ ወደ አእምሯችን ሊመጣ የሚገባው፣
ያሏቸው ጥሩ ጥሩ ባሕርያትና ያደረጓቸው መልካም ነገሮች ሊሆኑ ይገባል።
ልባችንን ስንመረምር የዚህን ዓለም አስተሳሰቦች አውጥተን መጣል ይኖርብናል።
ለምሳሌ ቅናትና ምቀኝነትን!
በአንጻሩ ደግሞ ጥሩ ጥሩ ባሕርያትን ማዳበር አለብን።
እንደ ፍቅርና ይቅር ባይነት ያሉትን!
እንግዲያው ሁላችንም ይሖዋ ከዚህ በፊት ያደረገልንን ነገርና አሁን እያደረገልን ያለው ነገር እናስታውስ።
አንድ ነገር እርግጠኛ እንሁን።
የማስታወስ ችሎታችንን በጥበብ ከተጠቀምን የሚያጋጥሙን ነገሮች ሁሉ በተሳካ ሁኔታ መወጣት እንችላለን!
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት በተጨማሪ
በዘመናችንም የማስታወስ ችሎታቸውን በጥበብ የተጠቀሙ ብዙ ምሳሌዎች አሉ።
ከእነዚህ መካከል አንዱ ወንድም ዶን ሽዌኒንግ ነው።
ይሖዋን በገለገለባቸው ረጅም ዓመታት በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ብዙ ለውጦች ሲደረጉ አይቷል።
ታዲያ ይህ ምን አስተምሮታል?
የይሖዋ ድርጅት ባለፉት መቶ ዓመታት ብዙ እድገት አድርጓል።
ብዙ ለውጦችና ማስተካከያዎችን አስተናግዷል።
እኔም ብዙ አስደናቂ ለውጦች ሲደረጉ አይቻለሁ።
እርግጥ አንዳንዶቹ ትንሽ የሚያስፈሩ ነበሩ።
ግን ሁሌም ውጤታቸው ያማረ እንደሆነ አስተውያለሁ።
ይሖዋ መዳብን በወርቅ ሲተካ አይቻለሁ።
ዶን ሽዌኒንግ እባላላሁ።
ይሖዋን ማገልገል ከጀመርኩ ከ70 ዓመት በላይ ቢሆነኝም
አገልግሎቴን ገና መጀመሬ ነው።
አባቴ እውነትን ያገኘው የሥራ ባልደረባው የሰጠውን መጽሐፍ አንብቦ ነው።
ብዙም ሳይቆይ ቤተሰባችን ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ።
ትልቅ ለውጥ ነበር።
ግን ጉባኤው ሞቅ አድርጎ ስለተቀበለን እንግድነት አልተሰማንም።
ወንድሞች የጉባኤው አካል እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አድርገዋል።
ስብሰባዎችን በጣም ወደድኳቸው።
በጉባኤ ውስጥ ቦታ እንዳለኝ ማወቄ አስደሰተኝ።
በድርጅቱ ወስጥ የተደረጉትን አንዳንዶቹን ለውጦች መረዳትና መቀበል ቀላል ነበር።
ለመጀመሪያ ጊዜ የአዲስ ዓለም ትርጉም ቅጂን ማግኘት ትልቅ ለውጥ ነበር።
በጣም ስለወደድኩት በየዕለቱ አንድ አንድ ምዕራፍ አነብብ ነበር።
ቀደም ሲል አነብበው ከነበረው የኪንግ ጄምስ ትርጉም በተለየ ለመረዳት ቀላልና ግልጽ ነው።
ይሖዋ እውን እንዲሆንልኝና ልቀርበው እንደምችልም እንድገነዘብ ረዳኝ።
ስለዚህ ጥሩ መንፈሳዊ እድገት አደረግኩ።
በ16 ዓመቴም ተጠመቅኩ።
ከተጠመቅኩ በኋላ በ18 ዓመቴ የጉባኤ አገልጋይ ሆንኩ።
መጀመሪያ ላይ ከተሰጡኝ ኃላፊነቶች መካከል አንዱ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን መምራት ነው።
በዕድሜም ሆነ በተሞክሮ የሚበልጡኝ ባሉበት ይህን ማድረግ አስፈርቶኝ ነበር።
ሁላችሁም ስለ መጣችሁ እ . . . አ . . . አመሰግናለሁ።
እ . . .
አንዳንዴ በጣም ከባድ ነበር።
ምን እንደምል ይጠፋብኛል።
ስለዚህ በቃ ዝም ብዬ እየጠየቅኩ ብቻ ነበር የማልፈው።
ወንድሞችና እህቶች እንደፈራሁ ሲያስተውሉ ስሜቴን ተረድተው ያግዙኛል።
ይሖዋ አዲሱን ኃላፊነቴን እንድወጣ እየረዳኝ እንደነበር ይሰማኛል።
በድርጅቱ ውስጥ የሚደረጉት አብዛኞቹ ለውጦች እያንዳንዳችንን ይነኩናል።
በ1972 የተደረገው ማስተካከያ ለእኔ ትልቅ ለውጥ ነበር።
እስከዚያው ጊዜ ድረስ ቅድሚያውን ወስጄ ከጉባኤው ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን የማደርገው ብቻዬን ነበር።
ብዙ ካባድ ኃላፊነቶች ነበሩብኝ።
ከ1972 በኋላ ግን የሽማግሌዎች አካል እንዲኖር ተደረገ።
ለውጡን መቀበል ከብዶኝ ነበር።
ይህም የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል።
በለውጡ ደስተኛ መሆን ብፈልግም ለእኔ ቀላል አልነበረም።
ስለጉዳዩ ወደ ይሖዋ በጣም ብዙ ጊዜ ሰለጸለይኩና እንዲረዳኝ ስለጠየኩት ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንደቀረብኩ ይሰማኛል።
ነገሮችን በይሖዋ ዓይን ማየት እንዳለብኝ ተምሬያለሁ።
በጊዜ ሂደት ለውጡ ያስፈለገው ለምን እንደሆነ ተገነዘብኩ።
የሽማግሌዎች አካል መኖሩ ጥሩ ለውጥ ነው።
ምክንያቱም ጉባኤውን የመንከባከቡ ኃላፊነት በአንድ ወንድም ላይ ብቻ አይወድቅም።
እንዲህ መሆኑ በጣም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል።
በዕድሜ የገፉት ካካበቱት ተሞክሮ፣ ወጣቶች ደግሞ ካላቸው ጉልበት ብዙ ተጠቅሜያለው።
‘ብዙ አማካሪዎች ባሉበት ስኬት ይገኛል’ የሚለው የምሳሌ ጥቅስ እውነት መሆኑን አይቻለሁ።
ምንጊዜም ቢሆን ለውጦች ይኖራሉ።
በዚህ ጊዜ ከይሖዋ ጋር መተባበር ይኖርብናል።
መጀመሪያ ለእኛ ባይታየንም እንኳን እንዲህ ማድረጋችን እንደሚጠቅመን ይሖዋ ያውቃል።
የኋላ ኋላ ጥቅሙ ለእኛው ነው።
ገና ከፊታችን ታላላቅ ለውጦች ይጠብቁናል።
የምንገኘው በይሖዋ ሕዝቦች ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ወቅት ላይ ነው።
በተለይ ታዳጊዎች፣ ይህ አጋጣሚ እንዲያመልጣችሁ አትፍቀዱ!
ስለ ይሖዋ ድርጅት ይበልጥ ከማወቅና በድርጅቱ ውስጥ ከማገልገል ወደኋላ አትበሉ።
በጉባኤ ውስጥ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ።
ከሽማግሌዎቻችሁ ጋር ተቀራረቡ።
ሁኔታችሁ የሚፈቅድላችሁን ያክል ብዙ ሥራ ለመሥራት ራሳችሁን አቅርቡ።
ይሖዋ እንዲመራችሁ ፍቀዱ።
በእሱ ታመኑ!
በእርካታና በደስታ የተሞላ ሕይወት ይኖራችኋል።
በሉ እንግዲህ ቻው።
ብዙ ሥራ ስለሚጠብቀኝ ልሂድ።
በዛሬው ጊዜ ለምንገኝ ለአብዛኞቻችን ጉባኤን ከሽማግሌዎች አካል ነጥሎ ማሰብ ይከብዳል።
ወንድም ሽዌኒንግ ግን ይህን ዝግጅት መቀበል በጣም ከብዶት ነበር።
ታዲያ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዲኖረው የረዳው ምንድን ነው?
ስለሁኔታው አጥብቆ ጸልይዋል።
ለውጡ የተደረገበትን ምክንያት ለመረዳትም ጥረት አድርጓል።
ቀጥሎ ሁለት ቤተሰቦች ያገኙትን መልካም አጋጣሚ እንዲጠቀሙበት ጸሎት እንዴት እንደረዳቸው እንመልከት።
ልዑካንን በቤታቸው በእንግድነት መቀበላቸው ምን ጥቅም አስገኝቶላቸዋል?
በምንኖርበት በመድሂን ከተማ
በ2015 ልዩ የክልል ስብሰባ ተካሂዶ ነበር።
እኛም ልዑካንን እንድንቀበል ግብዣ ቀረበልን።
ግን በወቅቱ ብዙ ሥራ ስለነበረብኝ መሥራት ያለብኝን ሥራዎች እንኳ ለመጨረስ ቀኑ አይበቃኝም ነበር።
ልጃችን 11 ዓመቱ ነበር።
በዚያ ላይ ባለቤቴ ካጋጠማት ሕመም ገና ማገገሟ ስለነበር እንግዶችን በሚገባ ማስተናገድ እንደምትችል አልተሰማትም።
ስለዚህ ‘ይህን ልዩ መብት መቀበል አንችልም። ልዑካንን ለመቀበል ጊዜው አሁን አይደለም’ ብለን አሰብን።
ልጃን ይሖዋን እንዲወድና እሱን እንዲያገለግለው ለመርዳት
የምናደርገውን ጥረት እንዲባርክልን ሁልጊዜ ወደ ይሖዋ እንጸልይ ነበር።
ልጃችን ወደ ይሖዋ እንዲቀርብ ለማድረግ የሚያስችሉ ነገሮችን ለማድረግ እንጥራለን።
አንድ ቀን ባለቤቴ ‘ይሖዋ በልግስና ብዙ ነገር ሰጥቶናል።
እኛም እሱን በመምሰል ለወንድሞቻችን ልግስና ልናሳይ ይገባል’ አለችኝ።
ከዚያም ከጸለይንበት በኋላ እንግዶችን ለመቀበል የሚያስፈልጉትን ሥራዎችን ተከፋፍለን መሥራት ጀመርን።
ልዑካኑ ወደ ቤታችን ሲመጡ ከልብ የመነጨ ፍቅር አሳይተውናል።
ለበርካታ ዓመታት የምንተዋወቅ ነበር የሚመስለው።
አብረናቸው ጊዜ በማሳለፋችንና ይሖዋን ምን ያህል እንደሚወዱት በማየታችን ተበረታተናል።
ጥሩ መንፈሳዊ ልማዶች እንዳሏቸው ያስታውቃል።
ከእነሱ ጋር የመሠረትነው ወዳጅነትና ያደረግናቸው ጭውውቶች በልጃችን ላይ ጥሩ ተጽዕኖ አሳድረዋል።
አንድ ቀን ልጄ ወደ እኔ መጣና ‘አባዬ ልነግርህ የምፈልገው ነገር አለኝ’ አለ።
ይሖዋን ከልቡ እንደሚወደው ከነገረኝ በኋላ ‘አባዬ መጠመቅ እፈልጋለሁ’ አለኝ።
መለስ ብዬ ሳስበው እነዚያን ልዑካን በእንግድነት መቀበላችን የጸሎታችን መልስ እንደሆነ ይሰማኛል።
በልዩ ስብሰባው ወቅት አስደሳች ጊዜ ነበር ያሳለፍነው።
ከእነዚያ ወንድሞች ጋር አሁንም ወዳጆች ነን።
እየሄድን እንጠይቃቸዋለን።
እነሱን በእንግድነት ቤታችን በመቀበላችን በጣም ተደስተናል።
ፈጽሞ የማንቆጭበት አስደሳች ጊዜ ነበር!
ወንድሞችን በእንግድነት መቀበላችን የእኔም ሆነ የእናቴ ጸሎት መልስ ይሆናል ብዬ ፈጽሞ አልጠበቅኩም ነበር።
አብርሃም የማያውቃቸውን ሰዎች እንኳ በእንግድነት ተቀብሏል።
ሁልጊዜም እንግዳ የመቀበል ምኞት ስለነበረኝ ስለ ልዩ ስብሰባው ስሰማ
‘አሁን ይሄን ምኞቴን የማሳካበት አጋጣሚ አገኘሁ’ ብዬ አሰብኩ።
በዚያን ወቅት ቤታችን ውስጥ የተሟላ የቤት ዕቃ እንኳ አልነበረንም።
ያሉን መሠረታዊ ነገሮች ብቻ ነበሩ።
አለ አይደል ለመብላት፣ ለመተኛት የሚያስፈልጉት ብቻ።
የምግብ ጠረጴዛችንም ትንሽዬ ነበረች።
ግን ችግሩ ይህ ብቻ አልነበረም ።
በውሳኔያቸው ስላልተስማማሁ ‘አንድም ነገር ታግዘናለች ብላችሁ እንዳትጠብቁ’ ብያቸው ነበር።
እህቴ የይሖዋ ምሥክር አልነበረችም።
ትኩረቴ ሙሉ በሙሉ ያረፈው በትምህርቴና በሥራዬ ላይ ብቻ ነበር።
ብቸኝነት፣ የባዶነት ስሜት ስለሚሰማኝ ፈጽሞ ደስተኛ አልነበርኩም።
በእንግድነት የተቀበልናቸው ባልና ሚስት በጣም ደግና ትሑት ነበሩ።
ተጫዋች፣ አፍቃሪና የሚቀረቡ ናቸው።
ቤት ያፈራውን፣ ያቀረብልናቸውን የትኛውንም ምግብ ለመብላት ፈቃደኞች ነበሩ።
በጓደኝነት ረጅም ዓመታት አብረን እንዳሳለፍን እንዲሰማን ነው ያደረጉት።
እነዚያ ባልና ሚስት በጣም ደስተኞች እንደሆኑ ማስተዋል ችያለሁ።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ይሖዋን ማገልገላቸው እንደሆነ ገባኝ።
እናቴና እህቴ እንግዳ ተቀባዮች ስለሆኑ በጣም አመስጋኝ ነኝ።
ምክንያቱም ከእነዚያ ደስ ከሚሉ ሰዎች ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚ ያገኘሁት በዚህ ምክንያት ነው።
ይሖዋን ይበልጥ የማወቅ ጉጉት እንዲያድርብኝ አድርገውኛል።
በዚህ ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርኩ።
ዕድገትም አደረኩ።
መጋቢት 7, 2020 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።
ቤተሰባችን ከእነዚያ ባልና ሚስት ጋር ለዘላለም የሚዘልቅ ወዳጅነት መሥርቷል።
አሁንም ድረስ እንጠያየቃለን።
እንደውም ኢንቴርኔት ላይ የቡድን ቻት አለን።
‘ትልቅ ቤተሰብ’ የሚል ስም ሰጥተነዋል።
እንግዶቹን መቀበላችን አስደሳች ብቻ ሳይሆን ከይሖዋ ያገኘነው ልዩ በረከት ነው።
ጠንካራ ቤተሰብ፣ አዳዲስ ጓደኞች፣ ፈጽሞ ከአእምሯችን የማይጠፉ አስደሳች ትዝታዎች!
ለሌሎች መልካም በማድረግ ከምናገኛቸው በረከቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
እርግጥ ደስ የማይሉን ትዝታዎችም ይኖራሉ።
እንዲያውም ልንረሳቸው የምንፈልጋቸው ትዝታዎች ይኖሩ ይሆናል።
ቀጥሎ የሚቀርብልን ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን የሚል ርዕስ ያለው የማለዳ አምልኮ ንግግር ጠቃሚ ትምህርት ይዞልናል።
ያዕቆብ 3:2 “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን” ይላል።
ይህ ከብዙ ነገር ጋር በተያያዘ እውነት ነው።
ግን ያዕቆብ 3:2 በዋነኝነት የሚናገረው በንግግራችን ስለ መሰናከል
ወይም የግርጌ ማስታወሻው እንደሚለው በንግግር ስለምንሠራው ስህተት ነው።
እስከ ዛሬ የአንደበት አጠቃቀማችንን ለማሻሻል የሚረዱ ብዙ ጠቃሚ ምክሮችን አግኝተናል።
ምናልባት “እንዳመጣል አትናገር”፣ “አስበህ ተናገር” ወይም ደግሞ “ከመናገር በፊት በጥሞና አዳምጥ”
እንደሚሉት ያሉ አንደበታችንን ለመቆጣጠር የሚረዱ ምክሮች ትዝ ይሉን ይሆናል።
ግን አስታውላችሁ ከሆነ እንዲህ ያሉ ምክሮችን እያገኘንና
ጥቅማቸውን በሕይወታችን እያየንም ሌሎችን የሚጎዳ ነገር እንናገራለን።
አሊያም ደግሞ ጥፋታችንን ላለማመን ሰበብ እንደረድራለን።
ከዛ ‘ምነው አፌን በቆረጠው’ እንላለን።
ጥቅሱ ላይ ያዕቆብ ትኩረት የሚስብ አገላለጽ ተጠቅሟል።
እንሰናከላለን!
ስንራመድ የሆነ ነገር አደናቅፎን ብንወድቅ ሰው አየኝ አላየኝ እንላለን።
ያሳፍረናል።
ከወደቅንበት ስንነሳ መጀመሪያ የምናደርገው ምንድን ነው?
አሰናክሎ የጣለን ምን እንደሆነ ለማወቅ ዙሪያችንን እናያለን።
ምናልባት እንቅፋት ኖሮ ይሆናል።
ወይም የምንጓዝበት መንገድ አባጣ ጎርባጣ ሆኖ ስንራመድ ያደናቀፈን ያ ሊሆን ይችላል።
ወይም ደግሞ ትኩረታችን ስለተከፋፈለ ያደናቀፈን የራሳችን እግር ሊሆን ይችላል።
እኔ እንደዚህ ያጋጥመኛል።
አንዳንዴ ደረጃ እየወረድኩ ሐሳቤ ሌላ ቦታ ይሆንና የራሴ እግር አደናቅፎኝ ልወድቅ ያኩበት ጊዜ አለ።
አልፎ አልፎ ደግሞ ተሰናክለን የምንወድቀው አንድ ሰው ሆነ ብሎ ጠልፎ ስለጣለን ሊሆን ይችላል።
ዛሬ የምንነጋገረው በዚህ ላይ ነው።
በምሳሌያዊ ሁኔታ እንድንሰናከል ምክንያት በሚሆኑ ነገሮች ላይ።
ይህ ጠቃሚ ነው።
እያንዳንዱ የሚያሰናክለን ነገር የምንማርበት አጋጣሚ ይሰጠናል።
ስህተት ስንሠራ ቆም ብለን ማሰባችን ይጠቅመናል።
‘በወቅቱ መጥፎ ምላሽ እንድሰጥ ያደረገኝ ምንድን ነው?
ሌላ ጊዜስ የተሻለ ምላሽ መስጠት የምችለው እንዴት ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ።
ተገቢ ያልሆነ ነገር እንድንናገር ስላደረገን ሁኔታ ቆም ብለን ማሰባችን ለሌላ ጊዜ
ራሳችንን እንድናዘጋጅና የሚጸጽተንን ነገር ከመናገር ይልቅ ራሳችንን መግዛት እንድንችል ይረዳናል።
ግን ደግመን ደጋግመን በንግግራችን ተመሳሳይ ስህተት የምንሠራ ከሆነ ካሰናከሉን ነገሮች ተምረናል ሊባል አይችልም።
ተሰናክለን የምንወድቀው በጥርጣሬ፣ በፍርሃት፣ በኩራት ወይም በሌሎች ብዙ ምክንያቶች ሊሆን ይችላል።
እስቲ በሁለቱ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገን እነዚህን ምክንያቶች ለይተን ማስተዋልና
ማስወገድ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
የመጀመሪያው ምክንያት በጣም መተዋወቃችን ሊሆን ይችላል።
አንድን ሰው በደንብ ካወቅነው አክብሮት ማሳየት እንደማያስፈልገን ይሰማን ይሆናል።
የዛሬው የዕለት ጥቅሳችን ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ያሰፈረው ያዕቆብም ያጋጠመው ይህ ይሆናል።
እስቲ ለያዕቆብ የኢየሱስ ታናሽ ወንድም ሆኖ ማደግ ምን ሊመስል ይችል እንደነበር አስቡ።
ኢየሱስን ‘እናታችን ከሁላችን ይበልጥ እንድትወድህ ነው የምትፈልገው።
ፍጹም ነኝ ብለህ ነው የምታስበው አይደል?’ ብሎት ይሆናል።
አዎ ግን እኮ ፍጹም ነበር።
መጀመሪያ ላይ ያዕቆብ ኢየሱስ መሲሑ እንደሆነ አላስተዋለም ነበር።
አንዱ ምክንያት ኢየሱስ አብሮ አደጉ መሆኑ ሊሆን ይችላል።
ማርቆስ 3:21 ዘመዶቹ ስለ ኢየሱስ የነበራቸውን አመለካከት ይነግረናል።
ማርቆስ 3:21 እንዲህ ይላል፦
“ዘመዶቹ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ‘አእምሮውን ስቷል’ በማለት ሊይዙት መጡ።”
በእንግሊዝኛው የጥናት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው የጥናት ማስታወሻ
እንዲህ ብለው ከተናገሩት ዘመዶቹ መካከል ያዕቆብም ሊገኝበት እንደሚችል ይጠቁማል።
ሆኖም በኋላ ላይ ያዕቆብ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ እንሞክር።
1 ቆሮንቶስ 15:7
“ከዚያም ለያዕቆብ ታየ፤ ቀጥሎም ለሐዋርያቱ በሙሉ ታየ” ይላል።
ኢየሱስ ለያዕቆብ ተገልጦለት ሲወያዩ ያዕቆብ ምን ተሰምቶት እንደሚሆን አስቡት።
ቀደም ሲል ስለ ኢየሱስ በተናገራቸው ነገሮች ተጸጽቶ እንደሚሆን ግልጽ ነው።
አሁን ያዕቆብ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ተገንዝቧል።
እኛስ ሌላ ሰው ከምናናግርበት በተለየ የትዳር አጋራችንን ተገቢ ባልሆነ መንገድ እናናግራለን?
ምናልባት የቤተሰባችሁ አባላት እናንተን የሚያበሳጯችሁ የትኞቹ ነገሮች እንደሆኑ ስለሚያውቁ
የሚጸጽታችሁን ነገር እንድትናገሩ የሚያደርግ ነገር ያደርጉ ይሆናል።
አስበውበትም ሆነ ሳያስቡት።
በዚህ ጊዜ ‘የቤተሰቤ አባል ላልሆነም ሰው ተመሳሳይ ምላሽ ነው የምሰጠው?’ ብላችሁ ጠይቁ።
ካልሆነ በጣም የምትቀርቧቸውን ሰዎች ስለምትይዙበት መንገድና ሲያበሳጯችሁ ምን ምላሽ እንደምትሰጡ ማሰብ ያስፈልጋችኋል።
ተገቢ ያልሆነ ምላሽ እንድንሰጥ የሚያደርገንን ምክንያት ማስተዋልና ምላሻችንን ማስተካከል ሊያስፈልገን ይችላል።
በጣም መተዋወቃችን እንቅፋት እንዲሆንብን አንፍቀድ።
እንቅፋቱን እናስተውል፣ እንዘጋጅ፣ ከዚያ አካሄዳችንን እንቀይር።
ሁለተኛው ጥቃት እንደተሰነዘረብን ሲሰማ ነው።
በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ስንሆን ቁልፉ ነገር ‘እንዲህ እንዲሰማን ያደረገው ምንድን ነው?’ የሚለውን መለየት ነው።
እንደተጠቃን እንዲሰማን ያደረገው ምንድን ነው?
ቅናት? ኩራት? ወይስ ራስ ወዳድነት?
ወይም ደግሞ ከዚህ በፊት የተፈጠረ አለመግባት ትዝ ብሎን ይሆን?
ሁኔታውን ማጤናችን አሉታዊ ምላሽ እንድንሰጥ ያደረገንን ስሜት እንድናስተውል ይረዳናል።
ወደፊትም ተመሳሳይ ስሜት ሲሰማን ተገቢውን ምላሽ እንድንሰጥ ይረዳናል።
እስቲ አንዳንድ የምንሰጣቸውን ተገቢ ያልሆኑ ምላሾች እንመልከት።
ለምሳሌ እንዳልተደመጥን ሲሰማን በምላሹ በጩኸት መናገር።
እንዳልተከበርን ሲሰማን እኛም በምላሹ አለማክበር።
ያለ ጥፋታችን ስንወነጀል ምላሻችን ትክክል መሆናችንን ለማሳየት መሟገት።
ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ሲረዱን በምላሹ መበሳጫት፣ ማኩረፍ።
ያዕቆብ ምዕራፍ 3 መጨረሻ ላይ
እነዚህን አሉታዊ ስሜቶች በአዎንታዊ ስሜቶች መተካት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይነግረናል።
ያዕቆብ 3:14-18 እንዲህ ይላል፦
“ሆኖም በልባችሁ ውስጥ መራራ ቅናትና ጠበኝነት ካለ አትኩራሩ፤ እንዲሁም በእውነት ላይ አትዋሹ።
“ይህ ከሰማይ የሚመጣ ጥበብ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ምድራዊ፣ እንስሳዊና አጋንንታዊ ነው።
“ቅናትና ጠበኝነት ባለበት ሁሉ ብጥብጥና መጥፎ ነገሮችም ይኖራሉ።
“ከሰማይ የሆነው ጥበብ ግን [ከዚህ በኋላ ልናዳብራቸው የሚገቡ መልካም ባሕርያን ሲገልጽ]
“በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣
“ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት እንዲሁም አድልዎና ግብዝነት የሌለበት ነው።
ከዚህም በላይ የጽድቅ ፍሬ ሰላም ፈጣሪ ለሆኑ ሰዎች ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች ይዘራል።”
ስለዚህ ጥቃት እንደተሰነዘረባችሁ ሲሰማችሁ ምን ዓይነት ምላሽ እንደምትሰጡ ከአሁኑ አስቡ።
ጥሩ ምላሽ እንድትሰጡ በአእምሯችሁ ተለማመዱ።
በጣም ከምንቀርባቸው ሰዎች ጋር ስንነጋገር ውይይታችን ምን እንደሚመስልና
ለምንናገረው ነገር ምን ምላሽ እንደሚሰጡ መገመት እንችላለን።
ስለዚህ መጀመሪያ ላይ ባይሳካልን እንኳ ጥሩ ምላሽ መስጠት እስከምንችል ድረስ በአእምሯችን መለማመዳችንን እንቀጥል።
ምናልባት ከሰውየው ጋር የምታደርጉት ውይይት እንዳሰባችሁ ላይሆን ይችላል።
ግን ቀደም ብላችሁ ልምምድ ማድረጋችሁ፣ ስሜታችሁን ለመቆጣጠርና ዋነኛ ግባችሁን ለማሳካት ማለትም
ከሌሎች ጋር ባላችሁ ግንኙነት ሰላም ፈጣሪዎች እንድትሆኑ ይረዳችኋል።
እንዲህ ያለ የአእምሮ ልምምድና ቀደም ሲል ከሠራነው ስህተት መማራችን አንደበታችንን በተሻለ መንገድ ለመቆጣጠር ይረዳናል።
‘እያንዳንዱ እንቅፋት የመማር አጋጣሚ ይሰጠናል’ የሚለውን ለማጉላት
ያዕቆብ በምዕራፍ 3:6 ላይ የተጠቀመውን ምሳሌ እንመልከት።
እዚያ ላይ ምላስን ከእሳት ጋር አመሳስሎታል።
ሳታውቁት የእሳት ቃጠሎ እንዲነሳ ምክንያት ብትሆኑ ምን ይሰማችኋል?
እንደምታዝኑ ግልጽ ነው።
ከዛ ባለፈ ግን ቃጠሎ የተነሳበትን ምክንያት ለማወቅ ጥረት ማድረጋችሁ አይቀርም።
ምክንያቱን ማወቃችሁ ይጠቅማችኋል።
ምናልባት የሆነ ነገር ጥዳችሁ መርሳት እንደሌለባችሁ
ወይም የምድጃውን ኃይል አለልክ ከፍ ማድረግ እንደሌለባችሁ ትማራላችሁ።
ብቻ ለሌላ ጊዜ ትምህርት ይሆናችኋል።
ከቃላት ጋር በተያያዘ በምትሰናከሉበት ጊዜም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ትችላላችሁ።
ሁኔታው አጢኑ።
ሌላ ጊዜ ተመሳሳይ መጥፎ ምላሽ እንዳትሰጡ ምን ማድረግ እንደምትችሉ አስቡ።
እያንዳንዱ መሰናከል የመማር አጋጣሚ እንደሚሰጣችሁ ፈጽሞ አትርሱ።
በሠራናቸው ስህተቶች ከመብሰልሰል ይልቅ በምናገኘው ትምህርት ላይ ትኩረት ካደረግን
‘መጥፎ’ ከሚባሉ ትዝታዎቻችን እንኳ ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን።
የቤተሰብ ራሶች ከባድ ኃላፊነት አለባቸው።
ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ሁሉ ማሟላት ቀላል አይደለም።
ቁሳዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን።
አይዝሉም እጆቼ የሚል ርዕስ ያለው ቀጥሎ የምንመለከተው የሙዚቃ ቪዲዮ
አንድ አባት ሚዛኑን ለመጠበቅ ምን እንደረዳው ያሳያል።
አይዝሉም እጆቼ መቼም፤
ቢደክመኝም አለሁ ባምላኬ በርትቼ።
አይዝሉም እጆቼ መቼም፤
ደግሞ ’ነሳለሁ እጆቹን ይዤ።
እጆቹን ይዤ።
አብረከረከኝ ኑሮ ዳገቱ፤
ልቤን አዛለው ሐሳብ ጭንቀቱ።
ዘንድሮስ በዛ መውረድ መውጣቱ፤
በኔ አቅምማ እንጃ መገፋቱ።
ምን ብዝል ብደካክም፣ እጆቹን አልለቅም፤
ማረፊያዬ ነው ቤቱ፣ ከደጁ አልርቅም።
አይዝሉም እጆቼ መቼም፤
ቢደክመኝም አለሁ ባምላኬ በርትቼ።
አይዝሉም እጆቼ መቼም፤
ደግሞ ’ነሳለሁ እጆቹን ይዤ።
አይዝሉም እጆቼ መቼም፤
ደግሞ ’ነሳለሁ እጆቹን ይዤ።
አይዝሉም እጆቼ መቼም።
አቀበቱን ሲያይ ይህ ልቤ ፈራ፤
ጉብ ያለው ሁሉ መስሎት ተራራ።
በስጋት ብቻ ክንዴ ’ንዳይላላ፤
በጎውን ላስብ፣ ሐሳቤን ልግራ።
ምን ብዝል ብደካክም፣ እጆቹን አልለቅም፤
ማረፊያዬ ነው ቤቱ፣ ከደጁ አልርቅም።
አይዝሉም እጆቼ መቼም፤
ቢደክመኝም አለሁ ባምላኬ በርትቼ።
አይዝሉም እጆቼ መቼም፤
ደግሞ ’ነሳለሁ እጆቹን ይዤ።
አይዝሉም እጆቼ መቼም፤
ደግሞ ’ነሳለሁ እጆቹን ይዤ።
አይዝሉም እጆቼ መቼም፤
ደግሞ ’ነሳለሁ እጆቹን ይዤ።
ቢደክመኝም አለሁ ባምላኬ በርትቼ።
አይዝሉም እጆቼ መቼም፤
ደግሞ ’ነሳለሁ እጆቹን ይዤ።
የቤተሰብ ራሶች ይሖዋ ቤተሰባችሁን ለመንከባከብ የምታደርጉትን ሁሉ ያያል።
የምንለውን ያህል ቀላል ባይሆንም እጆቻችሁ እንዲዝሉ የማትፈቅዱ ከሆነ
ይሖዋ ቤተሰባችሁ በአንድነትና በደስታ እሱን እንዲያገለግል ይረዳችኋል።
ውድ ሀብት ለማግኘት ቆፍሩ ከሚሉት ቪዲዮዎች
ከንባባችን ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን ተምረናል።
አሁን ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የመጨረሻው የሆነውን የሚልክያስ መጽሐፍን እንመለከታለን።
ይሖዋ ‘አንጥረኛ’ ተብሎ መጠቀሱ ምን ያስተምረናል?
አሥራ ሁለቱን የትንቢት መጽሐፍት አጥንተን ልንጨርስ መሆኑ በጣም የሚገርም ነው።
ልክ ነሽ፣ ቤተሰብ አምልኳችን ላይ ስንጀምረው ረጅም ጊዜ የሚወስድ መስሎኝ ነበር።
የእኔን ቀልብ የሳበው ምን አንደሆነ ታውቃለህ?
እያንዳንዱ መጽሐፍ በተጻፈበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታ መመርመራችን ልቤን ነክቶታል።
የእኔንም ልብ ነክቶታል።
ታዲያ ከሚልክያስ መጽሐፍ ላይ ትኩረት የሚስብ ምን ነገር አገኘሽ?
የሚልክያስ ትንቢት ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የመጨረሻው ነው።
በጊዜ ቅደም ተከተልም ቢሆን የመጨረሻው መጽሐፍ ነው።
ይሖዋ እስራኤላውያንን በጣም ታግሷቸዋል።
በርካታ ነቢያትን በመላክ እርማት ሰጥቷቸዋል።
እነሱ ግን ይሖዋ የሚጠላውን ነገር ማድረጋቸውን ቀጠሉ።
ያውም በተደጋጋሚ!
ትክክል።
የመጀመሪያዎቹ ሁለት ምዕራፎች ሁኔታውን በግልጽ ያሳያሉ።
ሕዝቡ ይሖዋን አቃለዋል።
የሚያቀርቡት መሥዋዕት እንከን ያለበት ነበር።
አንዳንዶቹ ሚስቶቻቸውን ፈተዋል።
የጣዖት አምላኪዎችን ለማግባት ሲሉ!
ካህናቱም ቢሆኑ ቸልተኞች ነበሩ።
እውነቱን ለመናገር እኔ ብሆን ትዕግሥቴ ያልቅ ነበር።
የይሖዋ ትዕግሥት ግን አላለቀም።
ሚልክያስን የላከላቸው ለዚህ ነው።
አዎ ልክ ነህ።
መጽሐፉን ማንበቤን ስቀጥል አንዳንድ ቃላት ትኩሬቴን ስበውታል።
አንዳንድ ቃላት ያላቸውን ለየት ያለ ትርጉም ማወቄ ከጠበኩት በላይ ግንዛቤዬን አስፍቶልኛል።
እውነትህ ነው።
ትኩረትህን የሳቡት የትኞቹ ቃላት ናቸው?
ምዕራፍ 3 ቁጥር 3 ይሖዋ “እንደሚያነጥርና እንደሚያነጻ ሰው ይቀመጣል፤ የሌዊንም ልጆች ያነጻል” ይላል።
ትኩረቴን የሳቡት ‘ማንጠር’ እና ‘ይቀመጣል’ የሚሉት ቃላት ናቸው።
ኧረ።
አዎ፣ ከዚያም እነዚህን ሁለት ቃላት የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት ላይ ፈለግኳቸው።
እዚያ ላይ አንድ ጽሑፍ አገኘሁ።
የማመሳከሪያው ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦
“ጥንታዊው የማንጠር ሥራ ጊዜ ይወስድ ነበር።
ስለዚህ አንጣሪው የቀለጠው ብረት በደንብ እንደተወለወለ መስታወት እስኪያንጸባርቅና
መልኩ በውስጡ እስከሚታይ ድረስ ተቀምጦ ይጠብቃል።”
ይሖዋስ ቢሆን ያደረገው ነገር ተመሳሳይ አይደለም?
ልክ እንደ አንጥረኛው እስራኤላውያንን ጊዜ ሰጥቶ ጠብቋቸዋል።
መከራ እንዲደርስባቸው ፈቅዷል።
እርማት ሰጥቷቸዋል።
ነቢያቱንም በተደጋጋሚ ልኮላቸዋል።
በመንፈሳዊ እያጠራቸው ነበር።
በጣም ይገርማል።
ሰዎች ምንም ያህል ቢበድሉት መቼም ቢሆን ደግነት በጎደለው መንገድ አይዛቸውም።
ለውጥ ማድረግ እንዲችሉ በቂ ጊዜ ይሰጣቸዋል።
ተቀምጦ በትዕግሥት ያጠራቸዋል።
ይሖዋ እኛንም በደግነት ይይዘናል።
ይሖዋ የሚያጠራን በቃሉ ውስጥ በሚገኘው ምክር ወይም በሾማቸው ወንድሞች ሊሆን ይችላል።
የሚደርስብን መከራም ቢሆን ያጠራናል።
ምክሩ ቅር ሊያሰኘን መከራውም ሊከብደን ይችላል።
ምናልባትም መከራው ካሰብነው በላይ ሊቆይ ይችላል።
ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮች በመንፈሳዊ ያጠሩናል።
ትክክል።
በነገራችን ላይ ይህ ስለ ይሖዋ ባሕርይ ምን የሚያስተምረን ይመስልሻል?
ይሖዋ ሰዎች ሊለወጡ እንደሚችሉ ያውቃል።
ስለዚህ የማጥራቱ ሥራ ቀላል ባይሆንም ይህንን የሚያደርገው የሚያስገኘውን መልካም ውጤት ስለሚያውቅ ነው።
ከዚህ አንጻር ይሖዋ በመንፈሳዊ ሲያጠራን እየቀጣን ሳይሆን ፍቅር እያሳየን ነው ሊባል ይችላል?
አዎ!
ሚልክያስ ይህንን የትንቢት መጽሐፍ የጀመረው “‘እኔ ፍቅር አሳይቻችኋለሁ’ ይላል ይሖዋ” በማለት ነው።
የ2018 መጠበቂያ ግንብ ‘የማነበው ነገር ምን ስሜት ያሳድርብኛል?’ እና
“በሕይወቴ ተግባራዊ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?”
በሚሉ ጥያቄዎች ላይ እንድናሰላሰል ያበረታታናል።
ለማሰላሰል የሚረዱ ግሩም ጥያቄዎች ናቸው።
ደግሞም እኮ እውነትህን ነው።
ምክር መቀበል አንዳንዴ ይተናነቀናል።
ሆኖም ይሖዋ የሚገስጸን ስለሚወደን እንደሆነ ካስታወስን ምክሩን ለመቀበል አንቸገርም።
እኛ ዛሬ ላይ ባይታወቀንም ይሖዋ ወደፊት ምን ዓይነት ሰው እንደሚወጣን ያውቃል።
ራሴን እንዲህ ብዬ ለመጠየቅ እሞክራለሁ፦
‘ይሖዋ እንዲያጠራኝ ከልቤ እፈልጋለሁ?
‘ማሻሻል ያሉብኝ አንዳንድ ባሕርያት እንዳሉ አውቃለሁ።
‘ግን ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ እጸልያልሁ?
‘ከመጽሐፍ ቅዱስና ከድርጅቱ የማገኛቸው ምክሮች ወደ ልቤ ጠልቀው እንዲገቡ እፈቅዳለሁ?
‘ወይስ በቸልታ አልፋቸዋለሁ?
‘ይሖዋ መከራ እንዲደርስብኝ ሲፈቅድ በፈተናው ላይ ብቻ በማተኮር እመረራለሁ?
‘ወይስ መከራው ውስጤን እንዲያጠራው በመፍቀድ እንደ ገርነትና ትዕግሥት ያሉ ባሕርያትን ለማዳበር እጥራለሁ?
ይሖዋ ስለ ራሴ እንዳውቀው የሚፈልገው ነገር ይኖር ይሆን?’
ጥሩ ጥያቄዎች ናቸው።
ብረት ለረጅም ጊዜ በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ ሲያልፍ የማያስፈልጉት ነገሮች ከውስጡ ይወጣሉ።
እኛም ያጋጠመን መከራ፣ ስደት ወይም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ለረዥም ጊዜ ሲቆይ ከባድ ሊሆንብን ይችላል።
ከዚህም በላይ ውስጣችን እንዳሉ የማናውቃቸው ስሜቶችና ዝንባሌዎች እንኳ ገሃድ ሊወጡ ይችላሉ።
እኔም እንዲህ ያነ ነገር አጋጥሞኝ ያውቃል።
ግን ጥሩ ምላሽ አልሰጠሁም ነበር።
የሚጸጽቱኝን ነገሮች ተናግሬያለሁ።
ደስ የማይሉ ስሜቶች ተሰምተውኛል።
በመፈሳዊው ጎልማሳ ነኝ ብዬ አስብ ነበር።
አይዞሽ፣ ሁላችንንም ያጋጥመናል።
ምሳሌው በጣም የሚያጽናናን ለዚህ እኮ ነው።
ይሖዋ ጉድለቶቻችን ጎልተው የሚታዩበት ጊዜ እንዳለ ያውቃል።
ይህ የሚጠበቅ ነው።
ግን የሚያተኩረው በዚህ ላይ ሳይሆን እንደ ወርቅ ባለ መልካም ጎናችን ላይ ነው።
በመሆኑም ይሖዋ አንድ ዓይነት ድክመታችንን እንድናስተውል ሲረዳን ለመሻሻል የሚረዳ ግሩም አጋጣሚ አድርገን እንመልከተው።
ጥሩ ነጥብ ነው ያነሳኸው።
ይሖዋ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳልፍ የሚፈቅደው የተሻልኩ ሰው መሆን እንደምችል ስለሚያውቅ ነው።
እኔም ሆንኩ አንቺ እነዚህን ባሕርያት ስናሳይ ይሖዋ ምን ያህል እንደሚደሰት አስቢው።
ለሌሎች ባለን አመለካከትም የይሖዋን ባሕርያት ማንጸባረቅ እንችላለን።
‘መልካም ጎናቸው ይታየኛል?
‘እምቅ ችሎታቸውን አስተውላለሁ?
‘በአዲሱ ዓለም ውስጥ የተሻለ ማንነት እንደሚኖራቸው አስባለሁ?
ወይስ የሚታየኝ ጉድለታቸው ብቻ ነው?’
ልክ ነሽ።
ይሖዋ የሚወድላቸው ባሕርይ ይታየኛል?
ምናልባትም እኔን በጣም የሚያበሳጨኝ ባሕርይ አንዳንድ ጊዜ በጣም ጠቃሚ ሆኖ ሊገኝ ይችላል።
እስማማለሁ።
በትዳራችንም የሚጠቅመን ይመስለኛል።
ማተኮር የምፈልገው በድክመቶቻቸን ላይ ሳይሆን እንደ ወርቅ ባሉ መልካም ባሕርያቶቻችን ላይ ነው።
ይሖዋ የሚያየን ወደፊት የተሻሉ ሰዎች እንደምንሆን አድርጎ ነው።
በትዳር ውስጥ ያሳለፍነው ምንም ያህል ጊዜ ቢሆን እኔም ማተኮር የምፈልገው በዚህ ላይ ነው።
ይገርማል!
ከአንድ ጥቅስ ብቻ ይህን ሁሉ ተማርን።
በጣም እንጂ!
መጽሐፉ በተጻፈበት ጊዜ የነበረውን ዓውድ በመመርመር፣
ለየት ላሉ ቃላት ትኩረት በመስጠትና
ሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት እንደሆነ በማሰላሰል ብዙ ተምረናል።
ገና የሚቀረን ብዙ ነገር አለ።
ለምሳሌ የሚልክያስ ትንቢት ስለ መሲሑ ምን እንደሚል ማጥናት እንችላለን።
እውነትም ጠለቅ ያለ የትንቢት መጽሐፍ ነው።
ልክ ነሽ።
መሲሑ ከመምጣቱ በፊት የተጻፈው የመጨረሻ የዕብራይስጥ መጽሐፍ የሚልክያስ ትንቢት ነው።
ሆኖም መልእክቱ ዛሬም እጅግ አስፈላጊ ነው።
ሚልክያስ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ትንቢት ተናግሯል።
መጥምቁ ዮሐንስ ደግሞ ወደ ኢየሱስ ይመራናል።
በጣም ደስ ይላል።
የሚልክያስ መጽሐፍ ይሖዋ ለሴቶች ስለሚሰጠው ቦታስ ምን ያስተምረናል?
“ልዩ ንብረት” የሚለው አባባልስ ለእኔና ለአንቺ ምን ትርጉም አለው?
እኔ በበኩሌ ይህን መጽሐፍ በመመርመር ገና የምማረው ብዙ ነገር አለ።
እነዚህን ትንቢቶች መመርመራችን ፈጽሞ አያስቆጭም።
ስለ ይሖዋ ታማኝ ፍቅር፣ ምሕረት፣ አሳቢነትና ኃይል ተምረናል።
በሁሉም ምዕራፎች ውስጥ የይሖዋ ባሕርያት ተገልጸዋል።
ስለ ይሖዋ ብዙ መማር ችለናል።
እንግዲያው መቆፈራችንን እንቀጥል።
ከአምላክ ቃል የምንማረው ገና ብዙ ነገር አለ።
ታላቅ አንጥረኛ የሆነው ይሖዋ አምላካችን በግለሰብም ሆነ በድርጅት ደረጃ እንድንሻሻል በትዕግሥት ይረዳናል።
እስቲ ቆም ብላችሁ ራሳችሁን ‘ይሖዋ የተሻልኩ አገልጋዩ እንድሆን በግለሰብ ደረጃ እያጠራኝ ያለው እንዴት ነው?’ ብላችሁ ጠይቁ።
ውድ ሀብት ለማግኘት ቆፍሩ በሚሉት ቪዲዮዎች የ12 ነብያት ታሪክ ሕያው ሆኖልናል።
ቪዲዮዎቹ ሲዘጋጁ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በትክክል ለማሳየት ብዙ ልፋት ጠይቋል።
ለምሳሌ የእስራኤላውያንን መንደር፣ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን ወይም ሌሎች ቦታዎችን ለማሳየት።
ቪዲዮዎቹ እንዴት እንደሚዘጋጁ ማየት ትፈልጋላችሁ?
ቀጣዩን ቪድዮ እንመልከት፦
ማንኛውንም ቪዲዮ ስንሠራ ዓላማችን ማስተማር ነው።
ስለዚህ ልባቸውን መንካት ይኖርብናል።
ይህን ለማድረግ ለተመልካቾች በገሃዱ ዓለም ያለውን ሁኔታ ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን።
አንድን ፕሮጀክት ከመጀመራችን በፊት፣
‘ከዚህ በፊት የተጠቀምንበትን ቦታ እንጠቀም ወይስ ሌላ አዲስ እናዘጋጅ?’ የሚለውን መወሰን አለብን።
ምክንያቱም ይህንን ሥራ የምንሠራው ከመዋጮ በሚገኝ ገንዘብ ስለሆነ ምንም ነገር እንዲባክን አንፈልግም።
ወንድሞችና እህቶች መዋጮ የሚያደርጉት ጥረው ግረው ያገኘውን ገንዘብ ነው።
ስለዚህ ቪዲዮዎችን በምንሠራበት ወቅት
ይህን መዋጮ በአግባቡ መጠቀማችን በጣም አስፈላጊ ነው።
አዲስ የቀረጻ ቦታ ከመገንባታችን በፊት ያለንን ነገር መጠቀም እንችል እንደሆነ እናያለን።
አንዳንዴ በአቅራቢያው ያሉ ወንድሞችና እህቶች ቤታቸውን ለጊዜው እንድንጠቀምበት ይፈቅዱልናል።
ፈቃድ ካገኘን ደግሞ በሌሎች ቦታዎችም ላይ እንቀርጻለን።
አሊያም የቤቴል ይዞታዎችን እንጠቀማለን።
አንድ ቪዲዮ ላይ ሆስፒታል ውስጥ የሚቀረጽ ትዕይንት ነበረው።
ሆስፒታል ሄዶ ከመቅረጽ ወይም ሆስፒታል የሚመስል ነገር ከመገንባት ይልቅ
ወንድሞች በቤቴል ውስጥ የሆስፒታል መስኮት የሚመስል ቦታ አገኙ።
ስለዚህ ትዕይንቱን እዚያ ቦታ ላይ ለመቅረጽ ወሰኑ።
ከዚያ ሆስፒታል ውስጥ የተቀረጸ የአንድን ሕፃን ቪዲዮ ተጠቅመው ቪዲዮውን ሠሩ።
ሙሉን ትዕይንት ለመቅረጽ የሚያስፈልገው ይህ ነበር።
አንዳንድ ፕሮጀክቶችን ያለንን ቦታ ተጠቅመን መሥራት አንችልም።
ስለዚህ ለዚያ ቪዲዮ የሚሆን አዲስ ቦታ እናዘጋጃለን።
አዲስ የቀረጻ ቦታ ለመገንባት ሲወሰን ቡድኑ አንድ ላይ ይሰበሰብና ምን ምን ነገሮች መዘጋጀት እንዳለባቸው ይወስናል።
መልእክቱን ለማስተላለፍ ምን ምን ነገሮች እንደሚያስፈልጉ ዝርዝር ለመውጣት
ኃላፊነት ያለው አንድ ወንድም ከቡድኑ ጋር አብሮ ይሠራል።
ይህም ቦታውን ለሚገነቡት ወንድሞች እያንዳንዱ ትዕይንት
ምን ምን እንደሚያስፈልገው ግልጽ ያደርግላቸዋል።
ስለዚህ ለቪዲዮ ቀረጻው የግድ አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ብቻ ይገነባሉ።
አንድ ሕንፃ ሲገነባ፣
ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግል አድርጎ መሠራት የተለመደ ነው።
ለቪዲዮ የምንሠራው ግንባታ ግን የተለየ ነው።
በቀላሉ የሚነቃቀሉና የሚገጣጠሙ ሆነው የሚሠሩ ናቸው።
የሚሠሩት በጊዜያዊነት ቢሆንም በሚያምር መንገድ ነው የሚሠሩት።
የሚሠሩት ቁሳቁሶች የእውነት ቢመስሉም አገልግሎት የሚሰጡ ላይሆኑ ይችላሉ።
ለምሳሌ ኩሽና እንሠራ ይሆናል።
ሆኖም የኩሽናው ካቢኔት መሳቢያዎችና በሮች የማይከፈቱ ይሆናሉ።
ወደላይ የሚወስዱ ደረጃዎችን እንሠራ ይሆናል።
የላይኞቹን ክፍሎች ግን አንሠራም።
ደረጃውን የምንሠራው ቤቱ ፎቅ እንዳለው ለማስመሰል ነው።
እንዲህ ማድረግ፣ ጊዜና ገንዘብ ይቆጥባል።
ለቪዲዮ ቀረጻ የሚሆን ቦታ ስንገነባ ቀደም ብሎ የተሠሩ ጠፍጣፋ የሆኑ የእንጨት ግርግዳዎችን እንጠቀማለን።
በቀላሉ ለመገጣጠም የሚመቹ ናቸው።
እነዚህን ግርግዳዎች አንዴ ተጠቅመን አንጥላቸውም።
ለአንድ ፕሮጀክት እነዚህ ግርግዳዎች ተቀብተው ከነበረ
ወይም በላያቸው ላይ የተለጠፈ ነገር ካለ እናነሳዋለን።
ሚስማርም ሆነ ሌላ ነገር ካለ አብረን እንነቅላለን።
ከዛ ሌላ ጠፍጣፋ እንጨት በላዩ ላይ እናደርግበታለን።
ስለዚህ አዲስ ግድግዳ ሆኖ ማለት ነው።
እነዚህን ግድግዳዎች ከዘጠኝ ዓመት በላይ ተጠቅመንባቸዋል።
አዲስ ነገር ስንገነባ፣ ‘በሌላ ጊዜ ለምን ዓላማ ልንጠቀምበት እንችላለን?’ ብለን አስቀድመን እናስባለን።
ለምሳሌ “ይሖዋ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ” የሚለውን የሕዝቅያስን ድራማ ስንሠራ
ወንድሞች በቪዲዮ ላይ የምንጠቀምባቸውን ቁሳቁሶች መልስን መጠቀም እንድንችል አሳስበውን ነበር።
በቪዲዮ ላይ የተጠቀምንባቸውን እነዚህን ዕቃዎች ከአሥር ዓመትም በኋላ እየተጠቀምንባቸው እንገኛለን።
ስለዚህ እነዚህን ቁሳቁሶች በተለያየ መንገድ ለብዙ ጊዜ ለመጠቀም አስበን እንሠራለን።
ለምሳሌ ለኢዮስያስ ቪዲዮ የተጠቀምንባቸን ቁሳቁሶች ለነህምያና ለዳዊት ቪዲዮዎች ተጠቅመንባቸዋል።
ዘመናዊ የመማሪያ ክፍሎችን ለማሳየት የተጠቀምንበትን የድሮ የመማሪያ ክፍሎችን ለማሳየትም ተጠቅመንበታል።
በተጨማሪም የደቡብ አሜሪካ ቤቶችን ለማሳየት ተጠቅመንበታል።
ለተለዩ ቪዲዮዎች የሚያገለግልም የስብሰባ አዳራሽ ገንብተናል።
ለቪዲዮ የሚመጥን የስብሰባ አዳራሽ ነው።
ሠላሳ ሰዎችን ብቻ ተጠቅመን አዳራሹን ሙሉ አስመስለን መቅረጽ እንችላለን።
የአዳራሹን ቤተ መጻሕፍትም ለሌላ ዓላማ ተጠቅመንበት እናውቃለን።
ለምሳሌ፣ የአንድ ሰው መኝታ ቤት ወይም ቃለ መጠይቅ የሚደረግበት ክፍል አድርገን እናዘጋጀዋለን።
ቁሳቁሶችን በድጋሚ ስንጠቀም
ተመልካቹ በድጋሚ እንደተጠቀምንባቸው እንዳያውቅ ጥረት እናደርጋለን።
ዕቃውን የምናስቀምጥበት መንገድ ለውጥ የሚያመጣው እዚህ ላይ ነው።
ጥቂት ወሳኝ ለውጦች ብቻ በማድረግ ተመልካቾች
ሌላ ቦታ ላይ እንደተሠራ እንዲሰማቸው ማድረግ እንችላለን።
ዓላማችን ትክክለኛና ማራኪ ቪዲዮ መሥራት ነው።
በተለይ ደግሞ ውስብስብ የሚመስሉ ነገሮችን
ቀለል ባሉ መንገዶች የሚሠሩበትን መንገድ መፈለግ በጣም ያስደስታል።
አንድን ችግር የመፍታት ችሎታና አቅም ካላቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር አብሮ መሥራት በጣም የሚያስደስት ነገር ነው።
ለዚያ ዓላማ ያልተዘጋጀን አንድ ቦታ ተጠቅመው በቪዲዮ ላይ በጣም ውብ ሆኖ እንዲታየን ያደርጋሉ።
ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ወንድሞቻቸውን ለመጥቀም ነው።
ይህ ደግሞ በጣም የሚያስደስት ነው።
ቪዲዮዎቻችን ከይሖዋ የተገኙ ግሩም ስጦታዎች ናቸው።
ቪዲዮዎቻችን የሚቀረጹባቸውን ቦታዎች ለማዘጋጀት
ምን ያህል ልፋትና የፈጠራ ችሎታ እንደሚጠይቅ ማየታችን አድናቆታችንን ከፍ አድርጎታል።
በዚህ ወር ፕሮግራማችን ላይ የማስታወስ ችሎታንን የምንጠቀምበት መንገድ ይሖዋን እንደሚያስደስተው ተምረናል።
ራሳችንን ከለውጦች ጋር በማስማማት፣
ለሌሎች መልካም በማድረግና
ይሖዋ እንዲያጠራን በመፍቀድ እሱን ማስደሰት እንችላለን።
በዚህ ወር ሰላምታ ይዘንላችሁ የመጣነው ከካምቦዲያ ነው።
ካምቦዲያ የምትገኘው በደቡብ ምሥራቅ እስያ እምብርት ላይ ነው።
በጣፋጭ ምግቦቿና በአስደናቂ ባሕሏ ትታወቃለች።
ተወዳጅ ምግባቸውን አሞክትሬን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በአቅራቢያቸው ካሉ የገበያ ቦታዎች ይሸምታሉ።
አሞክትሬ የሚዘጋጀው በተለያዩ ቅመሞች የተቀመመን ዓሣ በሙዝ ቅጠል ጠቅልሎ በማብሰል ነው።
ከከተሞች ወጣ ሲባልም የአገሪቱ ተፈጥሯዊ ውበት ይታያል።
በሰሜን ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል ትልልቅ ፏፏቴዎችን፣
በጥብቅ ደኖች ውስጥ ደግሞ ትላልቅ የእስያ ዝሆኖችንና ጋጋኖዎችን እናገኛለን።
በተጨማሪም በመላ አገሪቱ ማለት ይቻላል ሎተስ የተባለው የአበባ ዝርያ ይበቅላል።
ካምቦዲያ ዚርኮን የተባለው የከበረ ድንጋይ የሚገኝባት አገር ናት።
ራታናኪሪ ብሉ የሚባል ለየት ያለ ቀለም ያለው ዚርኮን ታመርታለች።
ይህ ለየት ያለ ቀለም የሚገኘው የከበረ ድንጋዩ በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ እንዲያልፍ ሲደረግ ነው።
በ1950ዎቹ መጨረሻ ሚስዮናውያን ወደ ካምቦዲያ መጥተው ምሥራቹን መስበክ ጀመሩ።
በ1965 በዚያ በነበረው አለመረጋጋት የተነሳ
ጆርጅና ካሮልድ ክራውፎርድን ጨምሮ ሁሉም ሚስዮናውያን አገሪቱን ለቀው ለመውጣት ተገደዱ።
እንዲያውም ለተወሰነ ጊዜ ያህል ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻልም ነበር።
በዚህም የተነሳ ለ25 ዓመታት ያህል ካምቦዲያ ውስጥ አንድም የይሖዋ ምሥክር አልነበረም።
እርግጥ ይሖዋ በካምቦዲያ ያሉትን ልበ ቅን ሰዎችን አልረሳቸውም።
በ1993 የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና አገኙ።
ሚስዮናውያንም ተመልሰው መጡ።
ዛሬ ከ33 ዓመታት በኋላ በካምቦዲያ ከ1,200 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ።
ይህ ደግሞ በአገሪቱ ውበትና ቅን ልብ ባላቸው ሕዝቦቿ ተማርከው
ከተለያየ አገር መጥተው በዚያ የሚያገለግሉትን በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች ይጨምራል።
1,400 የሚያህሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አሉ።
የአገሪቱ ነዋሪዎች ደስተኛና ልበ ቅን ስለሆኑ ወደዚያ የሚመጡ ሰዎች በቀላሉ የሚወዷቸው መሆኑ ምንም አያስገርምም።
በቅርቡ በአገሪቱ ውስጥ የመጀመሪያው የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተካሂዷል።
በትምህርት ቤቱ በ1999 ከጊልያድ የተመረቁ አንድ ባልና ሚስትን ጨምሮ 20 የሚያህሉ ወንድሞችና እህቶች ተካፍለዋል።
በካምቦዲያ ያሉ ወጣት ወንድሞችና እህቶች
ከእነዚህ ልምድ ያላቸው ሚስዮናውያን ጋር አብረው በመማራቸው ከፍተኛ ጥቅም አግኝተዋል።
ከእነዚህ ተመራቂዎች መካከል ሁለቱ በቻባ አምፓቭ ጉባኤ እንዲያገለግሉ ተመድበዋል።
የጉባኤው አስፋፊዎች 120 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ሰቫይ ሪን በተባለው ገለልተኛ ክልል ያገለግላሉ።
በዚያ ያለው ቡድን ከቻባ አምፓቭ ጉባኤ ጋር በቪዲዮ ኮንፍረንስ አማካኝነት ይሰበሰባል።
የጉባኤው አስፋፊዎችም በየተወሰነ ጊዜ ወደዚያ እየሄዱ ይሰብካሉ።
ወንድሞቻቸውንም ያበረታታሉ።
የቻባ አምፓቭ ጉባኤ አስፋፊዎችና
በሰቫይ ሪን የሚገኘው ቡድን አባላት
ሞቅ ያለ ክርስቲያናዊ ፍቅራቸውንና ሰላምታቸውን ልከውላችኋል።
በተለያዩ አገሮች ያሉ ወንድሞችና እህቶች ይሖዋን በትጋት ሲያወድሱ ማየት የሚያስደስት አይደለም!
ይህ ከይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚተላለፍላችሁ
JW ብሮድካስቲንግ ነው።